የድርጅቱ አጠቃላይ ገጽታ

ብኢኮ እንደ አዲስ የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ ከመደራጀቱ በፊት ሰባት ኮምፕሌክሶችን በመያዝ እና ወደ 5,000 የሰው ሀይል በማቀፍ የመከላከያ ኢንዳስትሪ ዘርፍ ተብሎ በዋናነት የመከላከያ  ትጥቆችን  በማደስና  በማምረት  ከፍተኛ  ሚና  ሲጫወት  የነበረ  ሲሆን  የተቋሙ አስተሳሰብና አሰራርም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቅኝት የነበረው በመሆኑ የቢዝነስ አስተሳሰብ አልነበረውም፡፡

የመከላከያ ኢንዳስትሪ ዘርፍ ሆኖ በሚሰራበት ጊዜ በርካታ ማሽኖችና የሰው ሀይል በትርፍነት የያዘ፣ የማምረት ፍላጎቱ ከፍተኛ የነበረ፣ እና በአደረጃጀት አለመስተካከል ምክንያት በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ያልገባ ስለነበር ይህን ለረጅም ጊዜ የተፈጠረ አቅምና የወታደራዊ አስተሳሰብ መልካም እሴቶችን እንደያዘ ወደ ልማት ብናስገባው የሚኖረው በጎ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ለሌሎች ነባር አምራቾችና አዳዲስ አምራች ኢንዳስትሪዎች አቅም ገንቢ አቅም ሆኖ እንዲያገለግል በማሰብ የነበሩትን የመከላከያ ትጥቅ አምራች ተቋማትና በልማት ድርጅትነት ተደራጅተው የነበሩ ፋብሪካዎችን በማካተት የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ ተቋቋመ፡፡ በሂደትም በአንዳንድ ኢንዳስትሪዎች ተጀማምረው የነበሩ ፕሮጀክቶችን በማሳደግ ራሳቸውን የቻሉ ኢንዳስትሪ ሆነው እንዲደራጁ በማድረግ በድምሩ አስራ አራት በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ አምራች ኢንዳስትሪዎችን በማደራጀት አቅሙን ያላገናዘበና እንዴት አቅሙን ማሳደግ እንዳለበትም ተገቢ ስልት ሳይነደፍለት ከአቅሙ በላይ ከፍተኛ ሀገራዊ ሃላፊነት እንዲሸከም ተደረገ፡፡

ኮርፖሬሽኑ አስራ አራት ኢንዱስትሪዎች አደራጅቶ ወደ ምርት ስራ ካስገባና በርካታ ፕሮጀክቶች በመያዝ የምርትና የግንባታ ስራዎችን ለመስራት እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ጊዜ የኮርፖሬሽኑ ቋሚና ኮንትራት ሰራተኛ በድምሩ ከአስራ ዘጠኝ ሺ በላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን ከገበያ መዳረሻ አንፃር ደግሞ በሀገር ውስጥ በሰባት ክልሎችና በሁለት ከተማ መስተዳድሮች የምርትና የግንባታ እንቅስቃሴ የነበረው ሲሆን ከውጭ የገበያ መዳረሻ አንፃር ደግሞ አምስት አገሮች ላይ በወታደራዊ ምርቶች አቅርቦትና የጥገና አገልግሎት ተሳትፎ ነበረው፡፡

ኮርፖሬሽኑ ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶችን ሳይጨርስ ለአሰሪ የመንግስት ተቋማት እንዲመልስ እንዲሁም አራት ወታደራዊ ኢንዳስትሪዎችን ለመከላከያ ሚ/ር እንዲመልስ በመንግስት መወሰኑን ተከትሎ ይህ እቅድ እስከተዘጋጀበት ግንቦት ወር 2012 ዓ.ም ድረስ በድምሩ ጊዜአዊ ሰራተኛን ጨምሮ ከአስር ሺህ በላይ የሰው ሀይል በስሩ አቅፏል፡፡

በትእዛዝ የሚመረቱ ምርቶች ሳይጨምር በአጠቃላይ በመደበኛነት 28 አይነት የምርት ምድቦችን የሚያመርት ሲሆን በእያንዳንዱ የምርት ምድብ ውስጥ በእስፔሲፊኬሽን የሚለያዩ ልዩ ልዩ ምርቶችን እያመረተ ለገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

በዚህ ረገድ በርካታ ምርቶች ለደንበኛ የተላለፉ ቢሆንም የምርት እሴት ጭማሪው አነስተኛ መሆኑ፣ የጥራት ጉድለት የነበረ መሆኑ፣ የምርት ብክነት በሰፊው የሚታይ የነበረ መሆኑ፣ የደንበኛ ትዕዛዝ ላይ ተመስርቶ ምርት የማይመረት መሆኑ፤ የምርት ስርጭቱ ለደንበኛ ተደራሽ ያለመሆን እና ከድህረ ሽያጭ አገልግሎት ጋር የነበሩ ጉድለቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የጎላ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ድክመት እና በጥቅሉ የአመራር ልምድ ማነስና ልማዳዊ የሆነ የአመራር አሰጣጥ ጉድለት ስለነበር በአመራሩ ምክንያት የነበረው ክፍተት ለኮርፖሬሽኑ ደካማ አፈፃፀም ትልቅ አሉታዊ ሚና ነበረው፡፡ ይሁንና ባለፉት ሁለት የሪፎርም አመታት ጉድለቱን ለማስተካከል በተደረገው ጥረት ተጨባጭ መሻሻሎች ታይተዋል፡፡

ሌላኛው ጉድለት ወጤታማ ተቋማዊ ስርዓት በመዘርጋትና በማዘመን በኩል የነበረው ጉድለት ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ባለፉት ሁለት የሪፎረም አመታት ይህን ጉድለት ለማስተካከል የሚያስችሉ መሻሻሎች ተከናውነዋል፡፡

ከሰው ሀይል አቅም ግንባታ አንፃር በየበጀት አመቱ የሚሰጡ በርካታ ስልጠናዎች የነበሩ ቢሆንም አብዛኛው ስልጠና መርሃ ግብርን ለማሟላት እንጂ የአፈፃፀም ጉድለትን የሚፈታና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያስችል ስላልነበረ ተጨባጭ መሻሻል ሊታይ አልቻለም፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ጉድለቶች በመከሰታቸው ምክንያት የተቋሙ ገፅታ የተበላሸ፣ ከፍተኛ እዳ ያለበት፣ እና በጥቅሉ የፋይናንስ ቁመናው ደካማ ነው፡፡

እነዚህን መረጃዎች እንደመነሻ ማስቀመጡ ተገቢ ቢሆንም ተቋሙ በአሁኑ ጊዜ ሰፋ ያለ የሪፎርም ስራ መስራቱን የቀጠለ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑን ተወዳዳሪ፣ ትርፋማ፣ እና የተቋቋመበትን አላማ ለማሳካት የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች ከላይ የተጠቀሱ ዳታዎች በአጭር ጊዜ የመለወጥ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *