የኢትዮ ኢንጂነሪነሪንግ የተቋቋመባቸው ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
- የማምረቻ ወይም የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ዲዛይን ማድረግ፣ መገንባት፣ በመፈተሽ ኮሚሽን ማድረግ፣ መጠገን፣ ማደስና ማሻሻል፤
- በኢትዮጵያ ሥነ ሐብታዊና ማኅበራዊ ዕድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ በሚችሉና የገበያ ክፍተትን ለመሙላት በሚረዱ በግንባታ፣ በማዕድን፣ በኃይል፣ በግብርና፣ በመጓጓዣ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ልዩ ልዩ የካፒታል እና የፍጆታ ዕቃዎችን እና መለዋወጫዎችን በማምረት፣ መጠገን፣ ማደስና ማሻሻል፤
- ምርትና አገልግሎቶቹን በአገር ውስጥና በውጪ አገራት መሸጥ እና የድህረ ሽያጭ
- አገልግሎቶችን መስጠት፤
- ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ፈጣን ልማት የሚያግዙ ተጨባጭና የወደፊት ፍላጐቶችን በማጥናትና በማልማት ምርትና አገልግሎትን የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማምረት፣ የቴክኖሎጂ አቅም ማስፋፋትና ማጎልበት በሚያስችል መልኩ ከትምህርት ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር እና ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ተቋማት ጋር በአጋርነት መሥራት፤
- በተሠማራባቸው የሥራ መስኮች ለሠራተኞቹ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት፣ በአገር ውሥጥም ሆነ ከአገር ውጭ ላሉ የምርትና አገልግሎት ተጠቃሚዎቹ እንዲሁም በዘርፉ ያላቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምድ ማዳበር ለሚሹ ኢትዮጵያውያንም ሆነ የውጭ አገር ዜጎች ሁሉ የማማከር አገልግሎት የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት፤
- የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትን ፖሊሲዎች ሕግጋትና መመሪያዎች መሠረት አድርጎ የገንዘብ ሚኒስቴርን በማሰፈቀድ ቦንድ መሸጥ፣ በዋስትና ማስያዝ፣ ከአገር ውስጥና ከውጪ አገር የገንዘብ ምንጮች የብድር ውል መደራደርና መበደር፤ እና
- የተቋቋመበትን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ የሚያስችሉ ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችን ማከናወን፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪነሪንግ ግሩፕ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ስር ከሚገኙ የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የነበረው ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ወታደራዊና የሲቪል ምርቶችን በማምረትና ተያያዥ የሆኑ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ ድርጅት ሲሆን ባለፉት ሁለት የለውጥ ዓመታት በመንግስት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተቋማዊ ለውጥ በማድረግ ወታደራዊ ክፍሉ ወደ ሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እንዲዞር፣ ሲቪል ክፍሉ ደግሞ እራሱን ችሎ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
የኮርፖሬሽኑ የቀድሞ አሰራሮች በርካታ ክፍተቶች የነበሩበትና የደንበኛ እርካታን ከሟላት አንፃር ችግር የነበረበት በመሆኑ አጠቃላይ ሪፎርም በማድረግ የነበሩበትን ክፍተቶች በመለየት በአመራርና በአሰራር፣በምርት ጥራት፣የድህረ ሽያጭ አገልግሎት፣የደንበኞች አያያዝና የአደረጃጀት ክፍተቶች ላይ በመስራት ኮርፖሬሽኑን ከስያሜው ጀምሮ ከመሰረቱ የሚቀይር ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በዚሁ መሰረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 475/2013 መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም በስሩ ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎችን በመያዝ ኢትዮ-ኢንጅነሪንግ ግሩፕ (ኢኢግ ወይም EEG) በሚል አዲስ ስያሜና ዓላማ ይዞ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡