ጠቅላላ መግለጫ

ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ ሰኔ 2 ቀን 2002 በብር 3,178,918604.55 በተከፈለ ካፒታልና በአስር ቢሊየን በተፈቀደ ካፒታል ከተደራጀ ጀምሮ በበርካታ የስራ ዘርፎች ማለትም በግዙፍ ፕሮጀክቶች ዲዛይንና ግንባታ፣ የገበያ ጉድለት አለባቸው በሚባሉ ምርቶች ዲዛይን ማድረግና ማምርት፣ የወታደራዊ ትጥቆች የእድሳት አገልግሎትና ምርት፣ እንዲሁም በሌሎችም መለስተኛ ስራዎች ተሰማርቶ  ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በእነዚህ ስራዎች ላይ የሚጠበቀውን ያክል ባይሆንም ከምርት አንፃር አወንታዊ ሚና ነበረው፡፡ ይሁንና በአመራር ብቃት ማነስ ምክንያት፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ድክመት፣ እና የሀገሪቱን የአሰራር ስርዓት ተከትሎ ባለመስራቱ ምክንያት ለከፍተኛ ውድቀት ተዳርጎል፡፡ ይህ በመሆኑም በኢኮኖሚያችን  ላይ  ቀላል  የማይባል  ጉዳት  እንዲደረስ  የበኩሉን  አሉታዊ  ሚና  መጫወቱ የማይታበል ሀቅ ነው፡፡

በሀገራዊ የተቋማት ሪፎርም ማዕቀፍ መሰረት የመንግስት ድርጅቶች የማሻሻያ ፕሮግራም ነድፈው ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን የዚህ ሀገራዊ ሪፎርም አካል የሆነው በብኢኮ ውስጥ ከ2010 መጨረሻ ጀምሮ እየተሰራ የሚገኘው የማሻሻያ ስራ የነበረውን ክፍተት የመለየት፣ ከተቋሙ አቅም በላይ የሆነውን የፕሮጀክት ስራ ለአሰሪው አካል የማስረከብ፣ አብዛኞቹን የትጥቅ አምራች ኢንዳስትሪዎች ለመከላከያ ሚ/ር ማስረከብ፣ በብኢኮ ውስጥ ታቅፈው እንዲቀጥሉ የተፈለጉ ኢንዳስትሪዎችንና ዋና መስሪያ ቤቱን መልሶ ማደራጀት፣ ሀብትና እዳ መለየት፣ ጥቅም ላይ ሳይውል በክምችት የነበረ ንብረትን መሸጥና የተቋሙን የስራ ማስኬጃ እጥረት ማቃለል፣ ተቋሙ የሚመራባቸውን መመሪያዎችና ፕሮስጀሮች መከለስና የአሰራር ስርዓቱን ማሻሻል፣ የወጭ ቅነሳ ፕሮግራም ማከናወን፣ የማምረት አቅም ያላቸውንና ደንበኛ ያላቸውን ኢንዳስትሪዎች በመለየት ልዩ ድጋፍ ማድረግና የማምረት ስራቸውን አጠናክረው እንዲሰሩ ማድረግ፣  የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችን በመለየት ለማስተካከል ጥረት ማድረግ፣ እና ከዋና ዋና ደንበኞችና ባለድርሻ አካላት ጋር ክፍተት የነበረውን ግንኙነት ማሻሻልና ተቀራርቦ መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ስራዎች እስከ አሁን የተከናወኑ ሲሆኑ እነዚህና ሌሎች ብኢኮን ለተልዕኮው የሚመጥን ተቋማዊ  ቁመና  እንዲኖረው  ለማድረግ  ጅምር  ስራዎች  ተጠናክረው  እንዲቀጥሉና  አዳዲስ ስራዎችም በፍጥነት እንዲከናወኑ የማድረግ ስራ በስፋት እና በልዩ ትኩረት አሁንም እየተሰራ ይገኛል፡፡

 

 

 

 

 

 

ከላይ የተጠቀሱት ስራዎችንና ሌሎችንም ተቋሙን ውጤትማና ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚከናወኑ ስራዎች ግልፅ በሆነ እቅድና እስትራቴጂያዊ በሆነ እይታ መመራት ስለሚኖርባቸው የአምስት አመቱ እስትራቴጂያዊ እቅድ ከዚህ ቀደም ከተዘጋጀው የብኢኮ የአስር አመት መሪ እቅድ ጋር እንዲናበብ የተደረገ ሲሆን በተወሰነ መልኩ ማሻሻያ ተደርጎበት እንዲዘጋጅ ተደርጎል፡፡

እቅዱ ለእቅዱ መነሻና ታሳቢ የሆኑ ጉዳዮችን፣ የውስጣዊና የውጫዊ ሁኔታ ግምገማና ትንተና፣ የተቋሙን እስትራቴጂያዊ ንድፈ ሃሳቦችና አቅጣጫዎችን፣ የትኩረት መስኮችን፣ እስትራቴጂያዊ ግቦችን፣ የእቅድ ዘመኑ እስትራቴጂዎችን፣ እስትራቴጂክ ማፕን፣  የሚሰሩ አበይት ተግባራትን፣ እና የአፈፃፀም መለኪያወችን አካቶ እንዲዘጋጅ ተደርጎል፡፡

የአምስት አመት እስትራቴጂክ እቅድ በቀጣይ አምስት አመታት የምናከናውናቸው አበይት ስራዎችና የምንተገብራቸው እስትራቴጂዎች በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሀገራዊ ሁኔታዎችን እና ለወደፊት የሚኖሩ እድገቶችና የገበያ ፍላጎቶችን ባገናዘበ መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን በየበጀት አመቱ የሚሰራው ስራ የሚመራበት ኦፕሬሽናል እቅድ ይህን ሰነድ እንደ መነሻ በመጠቀም የሚዘጅ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ይህ እቅድ ያለብዙሃኑ የነቃ ተሳትፎና ታታሪነት የሚሳካ አይደለምና ከከፍተኛው የብኢኮ አመራር እስከ እያንዳንዱ ሰራተኛ ድረስ የተቋሙ ከቀውስ መውጣትና እድገት በጥቅሉ ለሃገር የሚኖረው ፋይዳ ብቻም ሳይሆን ለእያንዳንዱ የተቋሙ አባልም የሚኖረው ሞራላዊና ቁሳዊ ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም በባለቤትነት ስሜት የድርሻውን ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *