ኢኢግ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር ስምምነት ተፈራረመ

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር የሲስተም ሰርተፊኬሽን ወይም ISO 9001:2015 ማግኘት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡
ስምምነቱ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስር በሚገኙት በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስት፣በፓወር ኢኩፕመንት ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣በአዳማ ግብርና ማምረቻ ማሽነሪ ኢንዱስትሪና በአዲስ ማሽንና መለዋወጫ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የሚተገበር ነው፡፡
በስምምነቱ መሰረት አራቱ ኢንዱስትሪዎች የሲስተም ሰርተፊኬሽን ወይም ISO 9001:2015 ያገኛሉ፡፡
ስምምነቱ ከተፈረመ ጀምሮ በአንድ አመት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል፡፡
ኢንዱስትሪዎቹ ሰርቲፋይድ መሆናቸው በሃገር ውስጥና በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ብለዋል የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ህይወት ሞሲሳ፡፡
ከሉላዊነት መስፋፋት ጋር በተያያዘ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ተወዳዳሪነት ከባድ መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊዋ ለጥራት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን በበኩላቸው በአጭር ጊዜ ውሰጥ በጋራ ያቀድነውን እናሳካለን ብለዋል፡፡ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለው አመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን በማመላከት፡፡
ጀርመንን በምሳሌት የጠቀሱት ሃላፊው የደረጃዎች ተቋምና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በተደረገው ስምምነት መሰረት ከደረጃዎች ኤጀንሲ በአራቱ ኢንደስትሪዎች የሚመደቡ ባለሙያዎች ለተግባራዊነቱ ስራቸውን ከነገ ይጀምራሉ፡፡
በተያዘው የበጀት አመት ኢንዱስትሪዎቹ ከኤጀንሲው ጋር ተቀራርበው በመስራት ወደ ውጤት እንደሚደርሱ ይጠበቃል፡፡
በግሩፑ ስር ከሚገኙት ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች ኢትዮጵያ ፕላስቲክስ ኢንዱስትሪ የሲስተም ሰርተፊኬሽን ያገኘ ኢንዱስትሪ መሆኑ ይታወቃል፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *