ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ጋር በጋራ ለመስራት ምክክር አካሄደ፡፡

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ጋር በጋራ በሚሰራባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር አካሄደ፡፡የተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች ውይይት አድርገዋል፡፡በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስር ከሚገኙት ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በብረታ ብረት ዘርፍ ስር የተደራጁት የአቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ኢንዱስትሪና የአዲስ ማሽንና መለዋወጫ ኢንዱስትሪዎች ላይ ገለጻ ተደርጓል፡፡የኢንዱስትሪዎቹ የማምረት አቅምና፣ የሚያመርቷቸው የምርት አይነቶች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡በውይይቱ ላይ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ህይወት ሞሲሳ የኢንዱስትሪዎቹን ምርታማነት ለማሳደግና የደንበኛ እርካታ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተከታታይ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ሃገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማዳን የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ ለተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች መለዋወጫዎችንና ሌሎች ምርቶችን ለማምረት እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር፣ከደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝም ተብራርቷል፡፡የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛህኝ ደቻሳ በበኩላቸው ኢንዱስትሪዎቹ ትልቅ የማምረት አቅም እንዳላቸው አስረድተው ድርጅታቸው በመለዋወጫ እጥረት ምክንያት የሚጠበቅበትን ያክል እያመረተ አይደለም ብለዋል፡፡ሃገሪቱ ከገጠማት የውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ መለዋወጫዎቹ በሃገር ውስጥ መመረት አለባቸው ብለዋል፡፡ይህንን ለመሻገር ሁለቱ ተቋማት ተቀራርበው ከሰሩ የጋራ ተጠቃሚነትንና ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡ሁለቱ ተቋማት የአቅርቦት አቅምንና ፍላጎትን በመለየት ውጤታማ ተግባር መፈጸም የሚያስችል የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *