ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ለሶማሌ ክልል መንግስት 162 ትራክተሮችንና 324 ተቀጽላዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ለሶማሌ ክልል መንግስት 162 ትራክተሮችንና 324 ተቀጽላዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱ በዛሬው እለት በጅግጅጋ ከተማ የተፈረመ ሲሆን ግሩፑን በመወከል ዋና ስራ አስፈጻሚው አምባሳደር ምስጋኑ አረጋና የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሃመድ ፈርመዋል፡፡
በግሩፑ ስር ከሚገኙት ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች አንዱ በሆነው በአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በመመረት ላይ የሚገኙትን የግብርና ማሽነሪዎች ለማቅረብ ነው ስምምነቱ የተፈረመው፡፡
አጠቃላይ ዋጋቸው ከ174 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡት ትራክተሮችና ተቀጽላዎች የክልሉን የግብርና እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ይጠበቃል፡፡
በፊርማ ስነ ስርአቱ ላይ የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ግሩፑ ከክልሉ ጋር በቅንጅት በመስራት ግብርናውን ለማዘመን ለሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በተለይ በግብርና ማሽነሪ አቅርቦት ሁለቱ ኣካላት ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ የድህረ ሽያጭ አገልግሎት ማእከል በክልሉ ለመገንባት ሁኔታዎች እንደሚቻችመም ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሃመድ በበኩላቸው በክልሉ ያጋጠመውን ድርቅ ያስከተለውን ጉዳት ለመቀነስና የኑሮ ውድነቱን ለማስተካከል በቀጣይ በጀት አመት ለግብርና ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው አስታውሰዋል፡፡
ስምምነቱም የዚህ እቅድ አካል ነው ብለዋል፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም በግሩፑ የቀረበው የድህረ ሽያጭ አገልግሎት ማእከል ግንባታ ማከናወን እንደሚቻል አረጋግጠዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *