ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የግብርና ማሽነሪዎችን በማምረት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሚኒስትር ተናገሩ፡፡
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው ግሩፑ እንደ መስኖና ቆላማ አከባቢዎች ሚኒስቴር ካሉ ተቋማትና ሌሎች በግብርና ዘርፍ ከተሰማሩ ተቋማትና ክልሎች የሚቀርቡ ፍላጎቶችን ለማሟላት ተግቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዛሬው እለት የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ለመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ያመረታቸውን 77 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የግብርና ማሽነሪዎችን በዛሬው እለት በይፋ ማስረከብ ጀምሯል፡፡
ርክክብ እየተፈጸመባቸው የሚገኙት ትራክተሮች 37 ሲሆኑ 30ዎቹ ትራክተሮች 120 የፈረስ ጉልበት ያላቸውና ማረሻም የተገጠመላቸው ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 7ቱ ደግሞ 180 የፈረስ ጉልበት ያላቸው እና ማረሻና መከስከሻ የተገጠመላቸው ናቸው፡፡
በዛሬው እለት ሰባት፣ 180 የፈረስ ጉልበት ያላቸው እና ማረሻና መከስከሻ የተገጠመላቸው ትራክተሮችን በይፋ የማረካከብ ስራ ተከናውኗል፡፡
ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በርክክብ ወቅቱ እንደተናገሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ወጣቶች በዘመናዊ መንገድ የእርሻ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል፡፡
በአማራ፣በኦሮሚያ፣በሶማሌ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኙ ወጣቶችን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
ወጣቱን ስራ ፈጣሪ እንዲሆን በማድረግ ሃገሪቱ ስንዴን ኤክስፖርት ለማድረግ እየሰራችው ለምትገኘው ስራ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንዳሉት ግሩፑ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በዘመናዊ መሳሪያዎች እንዲታገዝ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡
በቀጣይ በክልሎች የማምረቻ ፋሲሊቲዎችንና የድህረ ሽያጭ አገልግሎት የሚሰጡ ማእከላትን ለማቋቋም እቅድ እንዳለም አብራርተዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የአማራ፣የኦሮሚያ፣የሶማሌ እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የዘርፉ የቢሮ ሃላፊዎችና የወጣት ተወካዮች በመገኘት ማሽነሪዎችን በይፋ ተረክበዋል፡፡
ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ለአመታት በአሰራር ችግር ምክንያት ኢኮኖሚው ውስጥ ሳይቀላቀሉ የቆዮ ከ516 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የግብርና ማሽነሪዎችን በማምረት ወደ ኢኮኖሚው በማስገባት ላይ ይገኛል፡


