የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ክቡር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የአዲስ አመት መልእክት፡፡

የተከበራችሁ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የማኔጅመንት አባላትና መላው ሰራተኞቻችን፣ የተከበራችሁ ደንበኞቻችንና የተቋማችን ባለድርሻ አካላት እንኳን ለአዲሱ አመት ለ2015 አ.ም አደረሳችሁ አደረሰን!!
ተቋማችን ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ላለፉት አራት አመታት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል፡፡አሁንም ከደንበኞች፣ ከህዝቡና ከመንግስት የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ለመወጣት በጊዜ የለኝም መንፈስ በመስራት ላይ የምንገኝ ሲሆን ሁላችሁም የ2015 በጀት አመት እቅዳችን እንዲሳካ ከጎናችን በመቆም የተጣለብንን ሃላፊነት ለመወጣት ልንረባረብ ይገባል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት አመት የመጨረሻ ወራት ለእቅድ ዝግጅት ልዩ ትኩረት በመስጠት ሊሳካ የሚችል ግብ ጥለናል፡፡ይህም ተቋማችን የኖረበትን የኪሳራ ታሪክ በመቀየር ወደ ትርፍ ጎዳና ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ ለስኬታማነቱ የሁላችንንም ጥረት የሚጠይቅ ነው፡፡
ደንበኞች የሚረኩበትን ተቋም ለመፍጠር ‘’ ርካሽ ወድ ነው’’ ‘’cheap is expensive’’ በሚል መርህ ለምርቶቻችን ጥራት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራን እንገኛለን፡፡
በተሰማራንባቸው በብረታ ብረት፣ በኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ፣ በአውቶሞቲቭና ግብርና ማሽነሪ፣ በኮንስትራክሽን ማሽነሪ፣ በፕላስቲክና ፖሊመር ዘርፎች ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ለደንበኞች እርካታ መፈጠር ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

ክቡራትና ክቡራን !!
ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ በማድረግ ምርቱን በጥራትና በብዛት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ተደራሽ ለማድረግ ፣በዘርፉ የላቀ አፈጻጸም ካላቸው የውጭ ኩባንያዎች ጋር በተለያዩ አማራጮች በጥምረት ለመስራት ከምን ጊዜውም በላይ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡
ከዚህ አኳያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባደረግነው ርብርብ በትራክተር፣ ኮምባይነርና ፓምፕ ምርቶች ላይ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር የተፈራረምነው ስምምነት ተቋማችንን አንድ ደረጃ ከፍታ የሚያራምዱ እና ተቋማችንን በ2015 የአዳዲስ ፋብሪካዎች ባለቤት የሚያደርጉ በመሆናቸው ለተግባራዊነታቸው የሁላችንንም ድጋፍ የሚጠይቁ መሆናቸውን ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡
ይህን መሰሉ ስራና ጥረት በሁሉም ኢንዱስትሪዎቻችን ላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በአዲሱ አመት የአዲስ እይታ ባለቤት በመሆን ተቋማችንን ወደ ከፍታ ማማ በማሻገር በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሃገር የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንሰራለን፡፡
ክቡራትና ክቡራን!!
በግሩፓችን ከለውጡ አመታት በፊት የተሰሩት ስራዎች ሰፊ የሆነ የገጽታ ችግር ያመጣብን ቢሆንም ከዚህ ለመላቀቅ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን እየሰራን በመሆኑ በተለይም ደንበኞቻችን አጋርነታችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉና የመንግስት ባለ ድርሻ አካላትም እንደተለመደው ከጎናችን እንድትቆሙ በዚህ አጋጣሚ የአክብሮት ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

መልካም አዲስ አመት!!
ምስጋኑ አርጋ (አምባሳደር)
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *