በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የአሰሪና ሰራተኛ የህብረት ስምምነት ተፈረመ፡፡

በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የአሰሪና ሰራተኛ የህብረት ስምምነት ተፈረመ፡፡
የህብረት ስምምነቱን ግሩፑን በመወከል የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና ሰራተኛውን በመወከል የግሩፑ ሰረተኛ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ጉደታ ደንደና ፈርመዋል፡፡
በስነ ስርአቱ ላይ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣የግሩፑ ማኔጅመንት አባላት፣የአሰሪው ተደራዳሪ ኮሚቴና የሰራተኛ ማህበሩ ስራ አስፈጻሚዎች ተገኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንደገለጹት ተቋማት አትራፊና ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት በአሰሪውና በሰራተኛው መካከል ጤናማ የስራ ግንኙነት ሲኖርና ሰላማዊ የስራ ከባቢ ሲኖር ነው፡፡
የሁለቱ ጥምረት ሲኖር የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡
ሰራተኞች ተስፋ እንዲኖራቸው፤ተቋማት ተሻጋሪ እንዲሆኑ በሁለቱ መካከል ጤናማ ግንኙነት ሊኖር እንደሚገባ ያስታወሱት አምባሳደር ምስጋኑ የተቋም ባህል ለመቀየር የሁለቱ ቅንጅት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የህብረት ስምምነቱ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትንም ዋና ስራ አስፈጻሚው አመስግነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው ማህበሩ እንዲመሰረት እና የህብረት ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ለሰሩ የቀድሞ የግሩፑ አመራሮች እና ለአሁኑ አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አሁን የተፈረመው የቃል ኪዳን ሰነድ አሰሪውና ሰራተኛው በጋራ፣በቅንጅት ብዙ ፈተናዎችን እንዲያልፉና ውጤታማ ተቋም እንዲመሰርቱ የበኩሉን ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
በመተሳሰብና እጅ ለእጅ በመያያዝ ፣ችግሮች ሲኖሩም በጋራ በመፍታት መስራት የሚገባ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ካሳሁን ሃገራዊና አለም አቀፋዊ ተጽእኖዎችን መሻገር የሚቻለው በዚህ መልኩ ከተሰራ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግሩፑ የሰራተኛ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ጉደታ ደንደና ስምምነቱን ታሪካዊ ያሉት ሲሆን ሁሉንም አካላት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ለግሩፑ አመራሮችና ለኢሰማኮም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጠንካራ የሰራተኛ ማህበርና ገዢ የሆነ የህብረት ስምምነት እንዲኖር ላለፉት ሶስት አመታት በአመራሩና በሰራተኛው ሰፊና ተከታታይ ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *