የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን የፋይናንስ ሪፖርት በማጠናቀቅ ለኦዲት ለማቅረብ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው የስራ ሃላፊዎችና የግሩፑ የቦርድ አመራር አባላት በተገኙበት በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን ሂሳብ ማለትም ከመስከረም 19 ቀን/2013 አ.ም በፊት ያለውን ሂሳብ በመዝጋት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከተቋቋመበት ከመስከረም 20 ቀን 2013 አ.ም ጀምሮ ያለውን የጠራ ሂሳብ ለማጠናቀቅ ባለፉት የሪፎርም አመታት ሰፊ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡
በዚህ ስራም የቀድሞው ተቋምን ሂሳብ ለኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽን ተልኳል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን ሂሳብ በማጠናቀቅ ለኦዲት ዝግጁ የማድረጉ ጥረት ወደ ውጤት ስለመቃረቡና አበረታች ደረጃ ላይ ስለመድረሱ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የስራ ሃላፊዎች በውይይት መድረኩ ላይ አንስተዋል፡፡
የተቋሙን ካፒታል ማስተካከያን ጨምሮ ፤ በቀጣይ የጎደሉትን በማሟላት የተሰጡትን አስተያየቶች በማከል ማጠናቀቅና የጠራ ሂሳብ ለውጭ ኦዲት ማዘጋጀት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ አባል እና የፋይናንስ ስራውን እየደገፉ የሚገኙት አቶ አየለ ከበደ፤ የሂሳብ ስራውን የማጥራቱ ጉዳይ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን በመጥቀስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
የግሩፑ የሃብት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ም/ል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ገ/ማርያም የሂሳብ ስራውን እዚህ ደረጃ ለማድረስ ድጋፍ ላደረጉ የመንግስት አካላት ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን የተሰጡ አስተያየቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማካተተት ከጊዜው ጋር የሚሄድ የሂሳብ ደረጃ ላይ ለመድረስ እንሰራለን ብለዋል፡፡
በውይይቱ የኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጆች፣ የሃብት አስተዳደር ም/ል ዋና ስራ አስኪያጆች፣የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
