በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዳስትሪ 2 ሺህ የከተማ ባሶችን ለማምረት የሚያስችለውን ስምምነት ከቻይናው ዮቶንግ ኩባንያ ጋር በዛሬው እለት ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የዩቶንግ ኩባንያ በኢትዮጵያ ዋና ተወካይ ሚስተር ሉ ሻይ ናቸው፡፡
ስምምነቱ በግሩፑ ስር የሚገኘው የቢሾፍቱ አዉቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ 2 ሺህ ባሶችን ለማምረት የሚያስችልውን ግብአት በዋነኛነት እንዲያገኝ ያስችለዋል ፡፡ባሶችን ከማምረት በተጓዳኝ የስልጠና፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ይደረጋል፡፡ኢንዱስትሪው የሚያመርታቸውን ምርቶች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የሚያስችል ተግባርም ይከናወናል፡፡ግብአቶችን በሃገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ስምምነት ከመሆኑም በላይ የኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም የሚጨምሩ ዘመናዊ ፋሲሊቲዎችን ለመገንባት የድህረ ሽያጭ አገልግሎት ለማሻሻል የሚረዳ ነው፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በፊርማው ስነ ሰርአት ወቅት እንዳሉት ስምምነቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ችግር መቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የከተማውን የመጓጓዣ ችግር ሙሉ በሙሉ ባይቀርፍም፤ የበኩሉንና የራሱን ድርሻ ግን ይወጣል ብለዋል።
ሚስተር ሉ ሻይ በበኩላቸው ዩቶንግ ለስምምነቱ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀስ ገልፀዋል።

