የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በ2015 የበጀት አመት አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ገለጹ፡፡
በዛሬው እለት በኢንዱስትሪው የ2015 ዓ.ም አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንዲሁም የ2016 ዓ.ም እቅድ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የእውቅና ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ፕሮግራም ላይ የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ኢንዱስትሪው በ2015 የበጀት አመት ትርፋማ መሆኑን አስታውሰው ይህ ትርፍ እንዲመዘገብ ላስቻሉት የኢንዱስትሪው አመራሮችና ሰራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በቀጣዩ በ2016 በጀት አመት እንደ ግሩፕ የተለጠጠ እቅድ መያዙን ያስታወሱት አምባሳደር ሱሌይማን ለዚህ እቅድ መሳካት ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪው ሰራተኞች በተጠናቀቀው የበጀት አመት በቂ ግብአት ሳይኖር ያሉትን ውሱን ሃብቶች አሟጦ በመጠቀም ውጤት ማስመዝገብ ማሳየታቸውን በመግለጽ በዚህም ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡
በቀጣይ ግሩፑ ከመገጣጠም በመውጣት የራሱን ምርት በማምረት ወደ ገበያው ማስገባት አለበት ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ለዚህም ኢትዮጵያ የራሷ ብራንድ ይገባታል በሚል ስራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
ሰራተኛው ከተቋሙ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆንበት መዋቅር እየተሰራ መሆኑንም በማንሳት በአጠረ ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ለማስገባት ስራዎች እየተጠናቀቁ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
የእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬህይወት ትልቁ በበኩላቸው መንግስት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ማደግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን በመጥቀስ በመፍጠንና በመፍጠር በጋራ የተሻለ ውጤት እናስመዘግባለን ብለዋል፡፡
ከኢንዱስትሪው ያመረቷቸው ሃገር አቋራጭ አውቶብሶች ዘመናዊ መሆናቸውን በማስታወስ በዘርፉ ሚናቸውን እየተወጡ ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ በቀጣዩ በጀት አመት ከኢንዱስትሪው ከፍተኛ ውጤት የሚጠጠበቅ በመሆኑ ከሰራተኛው፣ ከደንበኞቻችን ጋር በጋራ በመሆን ለስኬታማነቱ ጠንክረው የሚሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በእለቱ አበረታች ውጤት ላስመዝገቡ የስራ ክፍሎች፣በኮምፓውንድ ካይዘን፣በንብረት ቆጠራና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ለሚገኙ አካላት የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ከኢንዱስትሪው ጋር በጋራ እና በቅርበት እየሰሩ ለሚገኙ በትራንስፖርት ዘርፍ ለተሰማሩ የኢንዱስትሪው ደንበኞች የሰርተፊኬትና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸለዋል፡፡
በተመሳሳይ ለኢንዲስትሪው ውጤታማነት ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ ለሚገኙት የግሩፑ ከፍተኛ አመራሮች እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡


