እንኳን ለአምራችነት ቀን አደረሳችሁ!
በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የአምራችነት ቀን በድምቀት ተከበረ።
ጷጉሜ 4/2015 ዓ.ም(ሀይሌ ግራንድ ሆቴል)
በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ “ኢትዮጵያ የራሷ ብራንድ ይገባታል!” በሚል መሪ ቃል የምክክርና ኤግዚቢሽን መርሃ ግብር ተካሄደ።
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በመክፈቻ ንግግራቸው “ኢትዮጵያ የራሷ ብራንድ ይገባታል” የሚል መሪ ቃል አንግበን የ 2016 በጀት አመት እቅድ ጀምረናል፤በመገጣጠም ከሚመረቱ የግብርና ማሽነሪ፣ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችና አውቶሞቲቮች መካከል ዋናዎቹን በሂደት በራሳችን አቅም በሀገር ውስጥ ለማምረት ትልቅ ራዕይ ሰንቀናል ያሉ ሲሆን ለዚህም ዕውን መሆን የመንግስትና የባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሃብታሙ ሃይለሚካኤል በእለቱ ባስተላለፉት መልዕክት የገበያ ጉድለት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ተፅዕኖ ለመቀነስ የግሩፑ ሚና ከፍተኛ ነው ያሉ ሲሆን፣ግሩፑ ያሳየው ውጤት የሚበረታታና ተስፋ የሚሰጥ ነው፤በቀጣይም ያሉት ተግዳሮቶች ላይ በመወያየት የመፍትሄ አቅጣጫ መቀመጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በእለቱ የተካሄደውን የፓናል ውይይት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት፣የስትራቴጂክ እቅድ እና ትራንስፎርሜሽን ሀላፊ እና የግሩፑ ቦርድ አባል ክብርት ዶ/ር እመቤት መለሰ የመሩ ሲሆን የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር እዮብ ተካልኝ፣የፕላንና ልማት ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታና የግሩፑ ቦርድ አባል ክቡር አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሃብታሙ ሃይለሚካኤል እንዲሁም የግሩፑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በፓናል ውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።
ይህ የፓናል ውይይት በዋነኝነት ግሩፑ ያለፉትን አመታት የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ፣ተግዳሮቶች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር የጋራ አቅጣጫዎች ማመላከት፣ግሩፑ ወደ አትራፊነት መሸጋገሩንና በቀጣይ በጀት አመት ትልቅ ግብ መቀመጡን እንዲሁም ደንበኞችና ባለድርሻ አካላት በግሩፑ ውጤታማነት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ ነው።
ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የምታደርገውን እንቅስቃሴም ለመደገፍ በትኩረት እንዲሰራበት አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመርሃግብሩ ላይ የግሩፑን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚዳስስ ገለፃ በግሩፑ ፕላንና ፕሮግራም ክፍል ሀላፊ አቶ መስፍን ተስፋዬ የቀረበ ሲሆን በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ ዶክመንተሪም ቀርቧል።
በእለቱም በተካሄደ ኤግዚብሽን በግሩፑ ስር የሚገኙት የዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች ምርት ቀርቦ ተጎብኝቷል።
ለግሩፑ አሁናዊ ለውጥ አስተዋፅኦ ላደረጉ ደንበኞች፣ባለድርሻ አካላት፣ለቦርድ አባላት፣ለኮሚቴዎች እንዲሁም ለኢንዱስትሪዎች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቷል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ምኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በመዝጊያ ንግግራቸው ግሩፑ የሀገራችንን ስም የሚያስጠራ ዘርፉን የሚያሻግር ምርቶች እንደሚያስገኝ ተስፋ የጣልንበት፣ ለመጪው ትውልድ ታሪክ የሚሰራባት ሀገር እንደምናስረክብ በማመን በጋራ ለውጥ ጉዞ የምንጀምርበት አመት እንደሚሆን በማመን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመድረኩ የግሩፑ ባለድርሻ አካላት፣ደንበኞች፣የዘጠኙ ኢንዱስትሪ የማኔጅመንት አባላት፣ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ጷጉሜ 4 “ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።






