በውይይት መድረኩ ላይ የግሩፑ ያለፉት የሪፎርም አመታት ላይ የተከናወኑ ተግባራት፣የተገኙ ስኬቶች እና ተግዳሮቶችን የሚያሳይ ጽሁፍ ቀርቧል፡፡
በዚሁ ጽሁፍ ላይ ግሩፑ ከገባበት ቀውስ በመላቀቅ እና በመንግስት የተጣለበትን ተልእኮ እንዲወጣ ለማስቻል የተከናወኑ ተግባራት ተዳሰዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ የውይይቱ አላማ አመራሩና ሰራተኛው ተቀራራቢ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ዋና ስራ አስፈጻሚው እንደ ሃገር ለማደግ ካስፈለገ ኢትዮጵያዊ ምርት ማምረት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ “ኢትዮጵያ የራሷ ብራንድ ይገባታል” በሚል መሪ ሃሳብ እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል፡፡
ይህንን እውን ለማድረግ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸው የተብራራ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የሰራተኛው ሚና ትልቅ ነው ተብሏል፡፡
መንግስት ግሩፑን ውጤታማ ለማድረግ በርካታ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት ሃላፊው ይሄው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የግሩፑ ስራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ከበደ ገለታ ቦርዱ ከሰራተኛ ጋር በአመት ቢያንስ አንድ ጊዜ ለመወያየት ያስቀመጠውን ግብ መሰረት ተደርጎ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በቀጣይ መሰል መድረኮችን በማዘጋጀት ከሰራተኛ ጋር ውይይት በማካሄድ ተቋሙን ውጤታማ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ሰራተኛውን በመወከል የቦርድ አባል የሚሆን የሰራተኛ ተወካይ ለመምረጥ አስር ሰራተኞች በእጩነት ቀርበው የተወዳደሩ ሲሆን ከኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ አቶ አስማማው አሰፋ በአብላጫ ድምጽ በመመረጥ ሰራተኛውን ወክለው የቦርድ አባል ሆነዋል፡፡
የውይይት መድረኩ የተመራው በግሩፑ የቦርድ አባላት በአቶ ከበደ ገለታ፣በዶ/ር በለጠ ስራብዙና በግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ነው፡፡








