አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር በቅርበት በመስራት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያችል ምክክር ኣካሄደ፡፡ሁለቱ ተቋማት የመግባቢያ ስምምነትን ተፈራርመው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባታቸው ይታወቃል፡፡በዛሬው የምክክር መድረክ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ ዩኒቨስቲ ለአንዱስትሪ በሚል መሪ ሃሳብ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ዩኒቨርስቲው የምርምር አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ችግር ፈቺ በሆኑ ምርምሮች ላይ ትኩረት በመስጠትና በጀት በመመደብ እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡በመሆኑም ለአንድ አመት የሚቆይ ፕሮግራም በመቅረጽ የኢንዱስትሪዎች ቁልፍ ችግር ላይ መፍተሄ የሚሰጥ ምርምር ለማካሄድ ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ከዚህም በተጓዳኝ በስልጠና፣ በላቦራቶሪና በትምህርት መስኮች የኢንዱስትሪውን አቅም ለመገንባት ከመቼውም ጊዜ በላይ መዘጋጀታቸውን ነው ያነሱት፡፡የኢንዱስትሪው አመራሮችና ባለሙያዎች በዩኒቨርስቲዎች በመገኘት የገለጻና የማማከር ስራዎችን ለመስራት የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋታቸውንም ፕሬዝደንቱ ተናገረዋል፡፡የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ህይወት ሞሲሳ ግሩፑ በዚህ ደረጃ ከዩኒቨርስቲው ጋር መተሳሰሩን በማድነቅ ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም ጋር በአጋርነት እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ራእይ ሰንቀን ተነስተናል ያሉት ኢንጂነር ህይወት ይህንን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል፡፡ግሩፑ የምርምርና ልማት፣የጥራትና የስልጠና ስራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎችንም በማጣቀስ ኢንዱስትሪዎችና ዩኒቨርስቲዎች ተቀናጅተው ከሰሩ የመንግስትን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችሉ ለውጦችን እያመጡ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከነበረበት ሰፊ ክፍተት አኳያ ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ እንደሆነ ያነሱት ደግሞ የግሩፑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚና የኦፕሬሽን ዘርፍ ሃላፊ ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ ናቸው፡፡የአይሶ ሰርተፊኬን ለማረጋገጥ በአምስት ኢንዱስትሪዎች ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን እንደማሳያነት የጠቀሱ ሲሆን አሁንም ሊፈቱ የሚገባቸው ቁልፍ ችግርች አሉ ብለዋል፡ዩኒቨረስቲው ላቀደው ችግር ፈቺ የምርምር ስራ ኢንዱስትሪው ምቹ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡በመሆኑም ዩኒቨርስቲውና ግሩፑ ተቀናጅተው መስራት ከቻሉ ምርታማነትን በማረጋገጥ ዘርፉን ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡