ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን ጠንካራ የቢዝነስ ተቋም ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትርና የግሩፑ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አብረሃም በላይ ተናገሩ፡፡
ዶ/ር አብረሃም ይህንን የተናገሩት በትናምትናው እለት ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ላምበረት በሚገኘው ሀይሌ ግራንድ በተከናወነው የአመራሮች ሽኝት እና አቀባበል ፕሮግራም ላይ ነው፡፡
ግሩፑን ሲመሩ የነበሩት አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ሆነው በመሾማቸው የተሸኙ ሲሆን አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ ወ/ሮ መሰረት ደስታ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚና የምርምርና ቢዝነስ ዴቬሎፕመንት ዘርፍ ሃላፊ፣ አቶ መሃመድ ጀማል ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚና የኦፕሬሽን ዘርፍ ሃላፊ ሆነው መመደባቸው ይታወቃል፡፡
በዚሁ ስነ ስርአት ላይ ዶ/ር አብረሃም ባስተላለፉት መልእክት ከለውጡ ወዲህ ግሩፑን ጠንካራ፣ አትራፊና ተወዳዳሪ የቢዝነስ ተቋም ለማድረግ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
በለውጡ ውስጥ ግሩፑን ለመምራት የተለያዩ አመራሮች መመደባቸውን በማስታወስ አሁን የተመደቡትም ለውጡን በማስቀጠል ውጤታማ ስራዎች እንደሚያሳኩ እምነቴ ነውም ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ ግሩፑ በርካታ ሃብቶችን የያዘ መሆኑን በማስታወስ ይህንን ሃብት ለሃገርና ለህዝብ ጥቅም ለማዋል እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው ግሩፑን ሊያዘምኑ የሚችሉ የተጀመሩት አዳዲስ ፕሮጀክቶች ከዳር እንዲደርሱ አደራ ብለዋል፡፡
የግሩፑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚና ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ክፍሌ ገ/ማርያም እንዳሉትም ግሩፑ በርካታ ተግዳሮቶችን አልፎ አበረታች ደረጃ ላይ መድረሱን በመግለጽ ከአዲሱ አመራር ጋር ያልተቆጠበ ጥረትን አጠናክሮ በማስቀጠል የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ተወካዮች ፣የስራ አመራር ቦርድ አባላት ፣የግሩፑ ማኔጅመንት አባላትና የሰራተኛ ማህበር ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡










