ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ባካሄዳቸው የሪፎርም ስራዎች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ሃይለሚካኤል ተናገሩ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን የተናገሩት የግሩፑ የ2015 አ.ም የስድስት ወራት አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ሲደረግ ነው፡፡
ግሩፑ ባቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት በኦፕሬሽን ስራዎች፣በፋይናንስና ሃብት አስተዳደር ስራዎች የሚበረታቱ ለውጦችን እያስመዘገበ ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለበት ሁኔታ የውስጥ አቅምን አሟጦ በመስራቱ የተሻለ ገቢ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡
የማሽኖች እርጅና፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢንዱስትሪዎቹ በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ተብለው በግሩፑ ሪፖርት የተካተቱ ናቸው፡፡
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ሃይለሚካኤል በውይይቱ እንዳሉት ግሩፑ ከነበረበት ዝቅተኛ አፈጻጸም በመላቀቅ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
የግሩፑ አፈጻጸም ላይ የታዩ ክፍተቶች በተያዘው የበጀት አመት መቀረፍ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
ተቋማቸው ግሩፑን ከዚህም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ግሩፑ ለሃገር የሚጠቅሙ ኢንዱስትሪዎችን የያዘ መሆኑን በማስታወስ ፤በሙሉ አቅማቸው ማምረት እንዲችሉ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ በመጥቀስ ጭምር፡፡
ግሩፑ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀምና የውጭ ምንዛሪን ለማዳን እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራን ለማስፋፋት የመንግስት አካላት ከግሩፓችን ጋር ተቀናጅተው በመናበብ ሊሰሩ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቋቋም ሰፕላየር ክሬዲትን አማራጭ ለማድረግ መታሰቡንም አብራርተዋል፡፡
የግሩፑን የቀጣይ ወራት እቅድ በመከለስ ውጤታማ ስራ ለመስራት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር ሱሌይማን ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር፤የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አመራሮችና ባለሙያዎች ፤የግሩፑ የቦርድ አባላት፤ የግሩፑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎችና የማኔጅመንት አባላት ተሳትፈዋል፡፡