በ2016 በጀት አመት የተያዘው እቅድ እንዲሳካ አመራሩና መላው ሰራተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ አሳሰቡ፡፡

በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በ2016 በጀት አመት የተያዘው እቅድ እንዲሳካ አመራሩና መላው ሰራተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅበት የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ አሳሰቡ፡፡
በዛሬው እለት የግሩፑ የሃብት አስተዳደር ዘርፍ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው አምባሳደሩ መልእክቱን ያስተላለፉት፡፡
በ2016 በጀት አመት በጥረት ሊደረስበት የሚችል እቅድ መዘጋጀቱን የገለጹት አምባሳደር ሱሌይማን ለስኬታማነቱ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ያሉንን ሃብቶች አሟጦ በመጠቀም፣የንብረት አያያዝን በማሻሻልና ቆጣቢ የሆነ የአስራር ስርአትን በመከተል የተያዘውን ግብ ማሳካት ይገባል ብለዋል፡፡
የግሩፑ የሀብት አስተዳደር ዘርፍ የ2016 ዓ.ም እቅድ ላይም በእለቱ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
ዘርፉ በ2015 ዓ.ም ያጋጠሙ ችግሮችን በመገምገም የነበሩትን ጠንካራ ጐን በመውሰድ የ2016 ዓ.ም ስራዎችን ያቀደ ሲሆን ይህንኑ ከኢንዱስትሪዎች፣ከመምሪያዎችና ከአገልግሎቶች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ የሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ መሠረት ደስታ በመሩት በዚህ መድረክ የሀብት አስተዳደር ዘርፉ በ2016 ዓ.ም በዋናነት ለመፈፀም ያቀዳቸውን ተግባራት ላይ ገለጻ ተደርጓል፡፡
የግብዓት አቅርቦትን ፈጣን ማድረግ፣ የውስጥ አሰራር ስርዓትን ማሳደግ፣ ዘመናዊ የኢንቨንተሪ ስርአት መዘርጋት፣ የጠራ የንብረት ቆጠራ ማድረግ የተደራጀ የመረጃ ስርዓት መዘርጋት፣ ከሜጋ ፕሮጀክቶች ጋር ያሉ የንብረት ርክክብና ሂሳብ ማስታረቅ ስራዎች ማጠናቀቅ በስፋት የተመከረባቸው የትኩረት ነጥቦች ናቸው፡፡
የግሩፑን ገቢ ሊያሳድጉ የሚችሉት ሁሉም መንገዶች ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ውይይት ተደርጓል፡፡ተሰብሳቢን እንደ ገቢ ምንጭ ወስዶ በትኩረት መሰብሰብና ለኦዲት ተጋላጭ የሚያደርጉ አሰራሮችን ክትትል ማድረግም በትኩረት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የሰፕላይ ቼይን ማኔጅመንት መምሪያ፣የሰው ሃብት አስተዳደርና ልማት መምሪያ እና የፋይናንስ መምሪያ ሃላፊዎች ገለጻና ማብራሪዎችን ሰጥተዋል፡፡
የሠራተኛ ድልድል አፈፃፀም መመሪያ፣ የስትራቴጂክ ሶርሲንግ መመሪያን ለማስገንዘብ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በእለቱ በብቃት መምራት በሚል ርእስ በዶ/ር ሙላቱ መብራቴ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
የዋና መ/ቤት የስራ ሃላፊዎች ፣የኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጆች እና የሃብት ዘርፍ ም/ል ዋና ስራ አስኪያጆች፣ የፋይናንስ እና የሰው ሃይል አስተዳደር ኃላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎች በመድረኩ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *