ጳጉሜን 2 / 2016 ዓ.ም/ኢኢግ/
ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ መሀል ሜክሲኮ የሚገኘውን ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች እና የግሩፑ አመራሮች በተገኙበት በዛሬው እለት አስመርቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የመንግስት ልማት ድርጅት ይዛታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ትዕግስቱ አምሳሉ ባስተላለፉት መልዕክት ግሩፑ የግሉ ተቋም የማይደርስባቸውን ዘርፎች በመያዝ ለሌሎች በር ከፋች ለውጥ ውስጥ መሆኑን ገልፀው ፣ግሩፑ የሚጠበቅበትን ተልዕኮ ለመወጣት በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ መግባት እንደሚገባው ገልፀዋል። አያይዘውም ተቋሙ እያደረገ ያለው ሪፎርም ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠር የስራ ተነሳሽነትን የሚጨምር በመሆኑ እየታየ ያለው ለውጥ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ሚኒስትርና የግሩፑ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አብርሃም በላይ እለቱ እንደ ሀገር ‘የሪፎርም ቀን ‘ ሆኖ እየታሰበ በመሆኑ ግሩፑ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተሰማራበት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የራሱን ለውጥ እያኖረ መሆኑን ጠቅሰው እያደረገ ያለው ለውጥ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልፀዋል።
ግሩፑ ከዚህ ቀደም ለስራና ለደንበኞች አመቺ ያልነበረና ለተቋሙ የማይመጥን እንደነበር አንስተው አሁን ላይ እያደረገ ባለው ሪፎርም ተስፍ ሰጪ ጉዞ ላይ እንደሚገኝ አንስተው፤ከዚህ ባለፈ መሠረታዊ የስራ ባህልና የዕይታ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ አንስተዋል።
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ተቋማችን ባለው አቅም እንዲያመርት ከጀመርነው እንቅስቃሴ አንዱ አካል የሆነው የዋናው መስሪያ ቤት እድሳት መሆኑን አንስተው በአዲስ መንፈስ ” ኢትዮጵያ የራሷ ብራንድ ይገባታል ” በሚል መሪ ቃል የያዝነውን አላማ ከግብ ለማድረስ ይህ ጥረት በር የሚከፍት ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የድርሻቸውን የተወጡ ለአዲስ አበባ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ዪንቨርስቲ፣የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ፣በግሩፑ ስር ለሚገኘው የብረታ ብረት ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ እንዲሁም የተቋሙ የምርምርና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ዘርፍ የዕውቅናና ሰርተፍኬት የማበርከት ስነ ስርአት ተካሂዷል።ህንፃው ባለ 5 ፎቅ እና ባለ 1 ፎቅ ሲሆን ሁለቱም የተገናኙበት ድልድይም 150 ሰዎችን መያዝ የሚችል አዳራሽ ነው። ዘመናዊና ምቹ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶች፣የሳውንድ ሲስተም የተገጠመላቸው ኮንፈረንስ ሩሞች፣ምቹ የእንግዳ ማረፊያ ቦታዎች ፣የመመገቢያ ቦታዎች ፣ መፀዳጃ ቤቶችን እና በቂ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራ ተካተውበታል።

















