በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀረበለትን የ3000 አውቶብስ ግዥ ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የግዢና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ላቀረበው የአውቶብስ ፍላጎት ግብዓት ለማሟላት ዓለም ዓቀፍ ግልፅ ጨረታ አውጥቷል፡፡
የተጠየቁት ተሸከርካሪዎች 2500 ባለ ዝቅተኛ ወለል (Low Floor) ሲሆኑ ቀሪዎቹ 500 አውቶቡሶች ባለ መካከለኛ ወለል (Middle Floor) ዘመናዊ የከተማ አውቶቡሶች ናቸው፡፡ አውቶብሶቹ በከተማዋ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ትራንስፖርት ፍላጎት ለማጣጣም በአጭር ጊዜያት ውስጥ ተመርተው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡
ኢንዱስትሪውም አውቶቡሶቹን አምርቶ ማስረከብ እስከሚጀምር ድረስ የከተማ አስተዳደሩ ያሉበትን የተሸከርካሪዎች ዕጥረት ለመቀነስ ከዚህ ቀደም ተመርተው በብልሽት ምክንያት የቆሙ የቢሾፍቱ አውቶብሶችን የመጠገን ስራ እያከናወነ ነው፡፡
ምንም እንኳን የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እንደልብ የመለዋወጫ መሳሪያዎችን ለማስገባት እክል ቢፈጥርም በተቻለ አቅም የጥገና ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ኢንዱስትሪው ከ 2004 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ተሸከርካሪዎችን አምርቶ ለደንበኞች ያስተላለፈ ሲሆን ከነዚህ ምርቶች መካከል በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የአንበሳ ከተማ አውቶቡስ ድርጅት እና ሸገር ብዙሃን ትራንስፖርት ድርጅት እየተጠቀመባቸው የሚገኙት ባለ ዝቅተኛ ወለል (Low Floor) እና ባለ መካከለኛ ወለል (Middle Floor) ባለ ቀይና ቢጫ ቀለም ዘመናዊ የከተማ አውቶቡሶች ተጠቃሾቹ ሲሆኑ በተመሳሳይ መልኩም የፐብሊክ ብዙሃን ትራንስፖርት ድርጅትም ባለ ሰማያዊ ቀለም ዘመናዊ አውቶቡሶቹን ማቅረቡ ይታወቃል፡፡