በኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የተመራ ቡድንም በግሩፑ ስር የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን እና ለባቡር መስረተ ልማት ዝርጋታ የተመረቱ ናሙና ምርቶችንም ጎብኝተዋል፡፡
በሁለቱ ተቋማት በጋራ የተዘጋጀው የ10 አመት የትብብር ማእቀፍ የቀረበ ሲሆን በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ በጋራ በሚሰሯቸው ስራዎች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
በማእቀፉ እንደተመላከተው የባቡር መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ፤ በባቡር ስራ እና በምርምርና ዴቬሎፕመንት ስራዎች ላይ በጋራ ስራዎች ይሰራሉ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንዳሉት የመንግስት ዋነኛ አላማ ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሪ የሚገቡትን ምርቶች በሃገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ ነው፡፡
በመሆኑም እንደ ፖሊሲ አስፈጻሚ ተቋም ለባቡር መሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚገቡትን መለዋወጫዎች እና ምርቶችን ሃገር በቀል በሆነው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ማምረት ያስፈልጋል፡፡
በሚቀጥሉት ከ5 እስከ 10 አመታት 5 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታ ለማካሄድ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በዚህ ስራ ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ኢንጂነር ታከለ ለኤ ኤም ጂ ሆልዲንግስ እየተዘረጋ የሚገኘው የውስጥ የባቡር መስመር ዝርጋታ ላይ ግሩፑ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኮ/ል ሸጋው ሙሉጌታ በበኩላቸው በግሩፑ ስር የሚገኙት ሶስት ኢንዱስትሪዎች በብረት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ እንደሆነ አስታውሰው ለመሰረተ ልማት ዝርጋታው የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ግሩፑ የሪፎርም ሂደት ላይ መሆኑን በመግለጽ የሚመርታቸውን ምርቶች በጥራትና በፍጥነት ለማቅረብ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ረገድ ሁለቱ ተቋማት ተደጋግፈው ከሰሩ ከውጭ የሚገቡትን ማስቀረት እንደሚቻል እምነታቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ከውይይቱ ባሻገር ለኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር የተመረቱ ናሙና የመለዋወጫ ምርቶች እና የኢንዱስትሪዎቹ የማምረቻ ፋሲሊቲዎች ተጎብኝተዋል፡፡













