ግሩፑ ባቀረበው አፈጻጻም በምርት፣ በሽያጭ፣ በገቢና በትርፍ የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡
ተቋሙ ያሉበትን የህግ ጉዳዮች በድርድር መፍታት በመቻሉ ከፍተኛ ወጪን መቀነስ መቻሉ እና ያልተወራረዱ የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦችን ማወራረድ መቻሉ ተብራርቷል፡፡
በግሩፑ ውስጥ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የኳሊቲ ማኔጅመንት ሲስተም እውቅና ሰርተፊኬት እንዲያገኙ መደረጉ እና የኢ.አር.ፒ ሲስተም ዝርጋታ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በግሩፑ አፈፃፀም ላይ ግብረ መልስ እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አቅርቧል።
በመጀመሪያው ግማሽ የበጀት አመት ያልተከናወኑ ስራዎችን በቀጣይ ስድስት ወራት ማጠናቀቅ እና የግሩፑን ሀብት ማወቅና በአግባቡ ለመጠቀም ያስችል ዘንድ የንብረት አስተዳደር ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ግብረ መልስ ተሰጥቷል።
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሸጋው ሙሉጌታ (ኮ/ል) በበኩላቸው በአጠቃላይ በግሩፑ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን አብራርተው በቀጣይ ስድስት ወራት ምርቶች ላይ እሴት መጨመር፤ የገበያ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ምርቶችን ማምረት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ጥቅም ላይ ያልዋሉ የግሩፑን ሃብቶች በመለየት የፋይናንስ ምንጭ ለማድረግም ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ግሩፑ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከፋይናንስ አንፃር ድጋፎችን ቢያገኝ ግብአት አቅርቦት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ወ/ሮ አስማ ረዲ በማጠቃለያቸው አዳዲስ ምርቶች ላይ ያለው ጅማሪ ጥሩ መሆኑን አንስተው በፕሮቶታይፕ ላይ ያሉ ምርቶች ተመርተው ወደ ገበያ መግባት እንዳለባቸው ገልፀዋል። የግሩፑ ሀብት ተሰብስቦና ተቆጥሮ በተደራጀ መልኩ መመዝገብ እንደሚገባውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ለግሩፑ ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
በወይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግና የግሩፑ ከፍተኛ የማናጅመንት አባላት እና አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡









