ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የጸሃይ ሃይል ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችለውን ምክክር አካሄደ፡፡
በዛሬው እለት ኢንተግሬትድ ፓወር ሲስተም እና ሬኒወብል ኢነርጂ ሶልሽን ከተባሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ምክክር ተካሂዷል፡፡
ግሩፑ ሰንዳፋ በሚገኘው የሶላር ፓኔል ማምረቻ ፋብሪካ ቅጥር ጊቢ ዘመናዊና አለም የደረሰበትን ማሽኖች በመትከል በአመት 500 ሜጋ ዋት ሃይል ለማምረት የሚያስችለውን ውይይት አድርጓል፡፡
በዚሁ ፕሮግራም ላይ የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንዳሉት የህብረተሰቡን የሃይል አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የጸሃይ ሃይል አንዱ አማራጭ በመሆኑ በዘርፉ በስፋት እንሰራለን ብለዋል፡፡
መንግስት ለሃይል ዘርፍ ትኩረት በመስጠቱ ግሩፑ የሃይል ማስተላለፊያ መሳሪያዎች ላይ በስፋት እንዲገባ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡
በዘርፉ ተወዳዳሪ በመሆን ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተጣለብንን ተልእኮ ለመወጣት እንሰራለን ሲሉም አምባሳደር ምስጋኑ ተናግረዋል፡፡
ከኩባንያዎቹ ዶ/ር ነዋይ አርጋው የሰንዳፋ ሶላር ፋብሪካ 500 ሜጋ ዋት በአመት የማምረት አቅም እንዲኖረው ሊገጠሙ የሚገባቸው ማሽነሪዎችን በማስመልከት ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም አሁን በፋብሪካው ከሚገኙ የማምረቻ ላይን ላይ 20 ሜጋ ዋት የሚመረትበት ሁኔታ ላይም ተወያይተዋል፡፡
አለም የደረሰበትን ዘመናዊ መሳሪያዎችን ወደ ሃገራችን በማስገባት ሰፊ፣ ጥራት ያለው ምርት በማምረት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የምናቀርብበት መንገድ ላይ ሰፊ ምክክር ተካሂዷል፡፡
የኩባንያዎቹ ሃላፊዎች በግሩፑ ስር የሚገኙ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን በመዘዋወር የጎበኙ ሲሆን በሶላር ፓኔል ምርቶች ላይ የእሴት ጭምሪ እንዲኖር የግሩፑ እህት ኢንዱስትሪዎች ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ኢትዮ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ከዚሁ በተጓዳኝ በጸሃይ ሃይል የሚንቀሳቀሱ መኪኖችን ቻርጅ የሚያደርጉ መሳሪያዎች ምርትና ተያያዥ ስራዎች ላይ በስፋት የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለ ተመላክቷል፡፡
በቅርቡ የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም የሁለቱ ተቋማት ሃላፊዎች ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡