የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ጋር ውይይት አካሄዱ፡፡
በውይይቱ ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳዩና የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን የስራ እንቅስቃሴን የሚዳስሱ ገለጻዎች ቀርበዋል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ስመ ጥር ከሆነ ኩባንያ ጋር በጋራ ለመስራት በመቻላችን ደስተኛ ነን ብለዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ልኡካን ቡድን አባላትም ግሩፑ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም እንችላለን ብለዋል፡፡
በግሩፑ በኩል ሊመረቱ የሚችሉ ለቴሌኮም መስመር ዝርጋታ የሚውሉ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች ሊመረቱ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ዝርዝር ምክክር ተካሂዷል፡፡
ግሩፑ ከኢትዮ ቴሌኮም ሊያገኛቸው የሚችላቸው ዘመኑ የደረሰባቸው የቴክኖሎጂና የኮሚኒኬሽን ውጤቶች እንዳሉ ተመላክቷል፡፡በጋራ መስራት ከተቻለም ሃገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን የሚቻልባቸው እድሎች መኖራቸውንም አመልክተዋል፡፡
በውይይቱ የብረታ ብረት ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ ታወር ክሬን፣ ኢትዮ ፕላስቲክ ማንሆል፣ ፓወር ኢኩፕመንትስ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የተለያዩ የሶላር፣የኤሌክትሪክና የትራንስፎርመር ምርትን እንዲሁም አቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የብረታ ብረት ውጤቶችን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ መስራት እንደሚቻል በኢንዱስትሪዎቹ ሃላፊዎች በኩል ገለጻ ተደርጓል፡፡
በቀጣይ ከሁለቱ ተቋማት የሚውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም እና የጋራ የስምምነት ሰነድ በማኖር ሊሰራ እንደሚችል አምባሳደር ሱሌይማን ተናግረዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ በኢትዮጵያ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ ጉብኝት ተደርጓል፡፡