የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የፋይናንስ ንኡስ ቦርድ በግሩፑ የተሰሩ የፋይናንስ የሪፎርም ስራዎች ላይ የመስክ ምልከታ ማካሄድ ጀመረ፡፡
ግሩፑ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት መስከረም 20/2013 ዓ.ም ላይ ሆኖ ያከናወናቸው የሂሳብ ማስተካከያ ሰራዎች ላይ ነው በኢንዱስትሪዎች በመዘዋወር ምልከታ እየተደረገ የሚገኘው፡፡
የሂሳብ ማስተካከያ ስራው የግሩፑን ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦችን ማጥራት ፣ኤል ሲ አድቫንስ እና ሌሎች የሂሳብ አይነቶችን ማጥራት፣ በክምችት ላይ የሚገኙ ንብረቶችን ፣ ቋሚ ንብረት እና ሌሎች ሃብቶችን ማጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ የግሩፑን ትክክለኛ የሂሳብ ቁመና ለማወቅ ባለፉት የሪፎርም አመታት ተከታታይ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡
በቅርቡ ለውጭ ኦዲተሮች ለማቅረብም ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡
በመሆኑም የግሩፑ የፋይናንስ ንኡስ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አየለ ከበደ፣ የግሩፑ ም/ል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ክፍሌ ገ/ማርያም በተገኙበት በአዲስ ማሽንና መለዋወጫ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ምልከታ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል፡፡
የዘጠኙም ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ ሃላፊዎችም በመስክ ምከታው ላይ ተገኝተው የአዲስ ማሽንና መለዋወጫ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የሂሳብ ስራ ላይ ውይይት በማድረግ ተሞክሮ ቀስመዋል፡፡
የስራው መጠናቀቅ ግሩፑ ከባንኮች ጋር፣ ከመንግስት የንግድ ተቋማት ጋር፣ ከውጭ ኩባንያዎችና ከሌሎች አካላት ጋር ግሩፑ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚያቀላጥፍለትና፣ ተወዳዳሪ የንግድ ተቋም ሆኖ ለመውጣት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያጠናክረለት ይጠበቃል፡፡
ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ ወደ ሪፎርም ስራ ውስጥ የገባው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፑ የሰራውን የሂሳብ ማጥራት ስራ ተከትሎ ፣ ከሪፎርም አመታቱ በፊት በነበረው የአሰራር ስርአት ችግር የነበረበት እዳ በመንግስት እንደተሰረዘለት ይታወቃል፡፡


