በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ፕሬዝዳንት የተመራ ቡድን በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስር የሚገኙትን ኢንዱስትሪዎች ጎበኘ፡፡

ቡድኑ በአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በሞጆ ዋየርና ኬብል ማምረቻ ፋብሪካ፣ በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ እና በአቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ጉብኝት አካሂዷል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እንደተናገሩት ግሩፑ ለሃገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ኢንዱስትሪዎችን ያቀፈ ነው፡፡
በዛሬው እለት የተጎበኙት ኢንዱስትሪዎችም ለግብርናው ዘርፍ፣ ለሃይል ዘርፍ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ፤ እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፍና የብረታ ብረት ዘርፉን ችግሮች የማቃለል አቅም ያላቸው መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ሃገሪቱ ከዘርፉ የምትጠብቀውን ለማበርከት ከባንኩ ጋር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው ባንኩ ድጋፍ እንደሚያደርግልን እናምናለን ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ደርቤ አስፋው በበኩላቸው ምርቶቹ ከውጭ የሚገቡትን የኢንዱስትሪ ምርቶች በማስቀረት ሃገሪቱ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎቹ የገጠማቸውን የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታትም በቀጣይ ቁልፍ የሆኑ ችግሮች ላይ በማተኮር የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ እና በጋራ የተጠቃሚነት መርህ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በጉብኝቱ የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንቶች እና ማናጀሮች እንዲሁም የግሩፑ ም/ል ዋና ስራ አስፈጻሚዎችና የማኔጅመንት አካላት ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *