ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በ2015 አ.ም ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆኑ ተገለፀ።

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በ2015 አ.ም ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ሃይለ ሚካኤል ተናገሩ፡፡
የግሩፑ የ9 ወራት የስራ አፈጻጸም የኤጀንሲው ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ግሩፑ ባቀረበው ሪፖርት ከምርት፣ ከድህረ ሽያጭ አገልግሎት፣ ከማያገለግል ንብረት ሽያጭና ከተለያዩ ገቢዎች ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
ግሩፑ ካሉት ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 5ቱ የተሻለ አፈጻጸም ቢያስመዝቡም ቀሪዎቹ በተለያየ ምክንያት ያቀዱትን ምርት ማሳካት እንዳልቻሉም ቀርቧል፡፡
ግሩፑ ምንም እንኳን ለጥሬ እቃ ግብአት በቂ የውጭ ምንዛሪ ባያገኝም ያሉትን ሃብቶች አሟጦ በመጠቀም የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጿል፡፡
በውይይቱ ወቅት የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ግሩፑ እንደ ሃገር ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን በማስታወስ የተጣለበትን ሃገራዊ ተልእኮ ከመወጣት አንጻር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ሊደረግበት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በግሩፑ ደረጃ አማራጭ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገዶችን በማፈላለግ እስከ 1 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን በአብነት ገልጸዋል፡፡
ያም ሆኖ ግሩፑ በጅምር የቀሩትን ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ለማስገባትና ትክክለኛ የአምራች ቁመናን ለመላበስ እንዲሁም ኢንዱስትሪዎቹን ለማስቀጠል ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ሃይለሚካኤል ግሩፑ ያከናወናቸው ስኬቶች ተስፋ የሚጣልባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የግሩፑ ቦርድ፣የማኔጅመንት አባላትና ሰራተኞች ባደረጉት ጥረት ተቋሙ እየተሻሻለ መምጣቱን በማስታወስ የኤጀንሲው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *