ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በተጠናቀቀው በ2015 የበጀት አመት ትርፍ ማስመዝገብ መጀመሩ ተቋሙ ተስፋ ሰጪ ጎዳና ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ መሆኑን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ተናገሩ፡፡
በግሩፑ የ2015 በጀት አመት አፈጻጸምና በ2016 በጀት አመት እቅድ ላይ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
በዚህ ውይይት እንደቀረበው ግሩፑ ከኪሳራ በመውጣት ትርፍ ማስመዝገብ መጀመሩ የሚበረታታ ሲሆን ይህንን ትርፍ በቀጣዩ በጀት አመት ማስቀጠል እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ያሉትን ሃብቶች አሟጦ በመጠቀም፣ተረፈ ምርቶችን መጠቀም እና የሃብት አጠቃቀምን ማሻሻል ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ጉዳዮች መሆናቸው ተለይቷል፡፡
ያም ሆኖ የውጭ ምንዛሪና የግብአት እጥረት የተቋሙ ፈተናዎች ሆነው ቀጥለዋል ተብሏል፡፡
በውይይቱ ላይ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ የግሩፑን ሁለንተናዊ ውጤታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
‘ኢትዮጵያ የራሷ ብራንድ ይገባታል’ በሚል የራሳችን ምርቶች እንዲኖሩን የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ አማራጭ የፋይናንስ እና የገበያ አቅርቦቶችን እያፈላለግን ነው ብለዋል፡፡
በቀጣዩ የበጀት አመትም በአዲስ መዋቅርና አደረጃጀት ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡
የግሩፑ የቦርድ ኣባል አቶ ሳሙኤል ሃላላ በበኩላቸው ግሩፑ ከገባበት ችግር በመውጣት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ቦርዱ ለቀጣይነቱ ያልተቆጠበ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ሃይለሚካኤል ተቋሙ ላለፉት ሶስት አመታት ከነበረበት ኪሳራ በመውጣት ትርፍ ማስመዝገብ መጀመሩ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣዩ የበጀት አመት የተያዘው የምርት እቅድና የትርፍ እቅድን ጠንክሮ በመስራት ለማሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡