ዛሬ መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ጋር በትብብር መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።
በስምምነቱ መሰረት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የባቡር መሠረተ ልማት መለዋወጫዎችን ያቀርባል።
ግሩፑ የተለያዩ ለባቡር መሰረተ ልማት ግብአት የሚሆኑ የብረታ ብረት፣ኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም የፕላስቲክ ምርቶችን ያቀርባል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ኢንዱስትሪዎች የሆኑት አዲስ ማሽንና መለዋወጫ ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣አቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ብረታ ብረት ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ፣የፓወር ኢኩመንትስ ማምረቻ ኢንዱስትሪና የኢትዮጵያ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪዎች እነዚህን የባቡር መሠረተ ልማት መለዋወጫ ዕቃዎች ያመርታሉ፡፡
ይህም የሀገሪቱን የባቡር ትራንስፖርት ለማሳደግ አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚያስችል በስፊርማ ስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
ስምምነቱ ተግባራዊ ሲሆን የባቡር መሠረተ ልማት መለዋወጫዎች እጥረት በመቅረፍ ኢትዮጵያ በመስኩ ለመለዋወጫ ግዥ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ያድናልም ተብሏል።
የመግባቢያ ሰነዱ በአስቸኳይ የጋራ የቴክኒክ ግብረ ሀይል ማቋቋምን የሚያካትት ሲሆን የግብረ ሀይሉንም ዝርዝር ተግባራት አስቀምጧል።ከዝርዝር ተግባራቱ ውስጥ ተቋማቱ በጋራ የሚሠሩዋቸውን ስትራቴጂያዊ ስራዎች በፍጥነትና ጥልቀት ለይቶ በማቅረብ ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ ነው።
ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በኩል የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ሲሆኑ በኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር በኩል ዋና ስራ አስፈጻሚው ዶ/ር አብዲ ዘነበ ፈርመዋል።