ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ትርፋማነቱን ማስቀጠሉ ተቋሙ እየተለወጠ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
ግሩፑ የ2016 በጀት አመት 1ኛ ሩብ አመት ሪፖርቱን ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር አቅርቧል፡፡
በሪፖርቱም በሩብ አመቱ ከ89 ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ መመዝገቡ የተገለጸ ሲሆን ትርፉ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ ያለው ቢሆንም ከእቅዱ አንጻር ግን መሻሻል የሚገባው መሆኑ ቀርቧል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የግብአት እጥረት ባለበት ሁኔታ የተመዘገበው ውጤት የሚበረታታ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
የውስጥ አቅምን አሟጦ መጠቀም እና የወጪ ቅነሳ ስራዎች ለተመዘገበው ውጤት በምክንያትነት የተጠቀሱ ናቸው፡፡
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በመጀመሪያው ሩብ አመት ያልተሳኩ ተግባራት ላይ የማካካሻ እቅድ በማውጣት በሚቀጥሉት ወራት ርብርብ እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡
ከምርት አንጻር በውስጥ አቅም ሰራተኛውን በማሳተፍ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
በግሩፑ በኩል ከግል ባንኮች ጋር በቅንጅት በመስራት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ እየተሰራ ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡
ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በጋራ ለመስራት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ከዳር ለማድረስ እና ተቋሙ በሰፕላየር ክሬዲት ግብአት እንዲያገኝ ለማስቻል ሰፊ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም ቀርቧል፡፡
በዘላቂነት ግን ከችግሩ ለመውጣት ከገጣጣሚነት አስተሳሰብ በመላቀቅ ወደ አምራችነት መሸጋገር እንደሚገባ አምባሳደር ሱሌይማን ያብራሩ ሲሆን ለዚህም ኢትዮጵያ የራሷ ብራንድ ይገባታል በሚል መሪ ሃሳብ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ባቀረበው ግብረ መልስ ግሩፑ ካሉት ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎቹ አብዛኛዎቹ ትርፋማ መሆናቸው፣የገጽታ ግንባታና የማህበራዊ ሃላፊነት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ፣የአደረጃጀት ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉና የፕሮጀክቶች ርክክብ ላይ የተሰሩት ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብሏል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሃብታሙ ሃይለሚካኤል ግሩፑ በሪፎርም ሂደት እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ለሃገሪቱ ያለውን ተስፋ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
በሩብ አመቱ ግሩፑ ከአስተዳደሩ ጋር የተፈራረመው እቅድ ላይ የተስተዋሉ ጉድለቶችን መሙላት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል፡፡
ግሩፑ ጳጉሜ 4 ቀን ያዘጋጀው መድረክ ከባለድርሻ ኣካላት ጋር ያለውን ትስስር የሚያጠናክርለት በመሆኑ በቀጣይ መሰል መድረኮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡
ከውይይቱ በተጨማሪ በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡
