ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በማፋክቸሪንግ ዘርፍ ያለው አቅም ለሃገሪቱ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማኔጅመንት አባለት ገለጹ፡፡
የማኔጅመንት አባላቱ በግሩፑ ስር ከሚገኙት ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪን፣የሞጆ ዋየርና ኬብል ማምረቻ ፋብሪካን፣የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪንና የአቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ማምረቻ ኢንዱስትሪን ተዘዋውረው ጉብኝተዋል፡፡
የንግድ ባንክ የማኔጅመንት አባላቱ የአዳማ ግብርና ለእርሻው መዘመን ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ባንኩ በግብአት አቅርቦት ረገድ ትልቅ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡
ባንኩ አርሶ አደሩን መሰረት ያደረጉ፣ግብርና ላይ የሚሰሩ ስራዎችን መደገፍ ቀዳሚ ተልእኮው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቀላልና ከባድ ተሸከርካሪዎችን፣የከተማና ሃገር አቋራጭ አውቶብሶችን ጨምሮ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን እያመረተ የሚገኘው ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪም ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪን የማዳን አቅም ያለው በመሆኑ ባንኩ ከኢንዱስትሪው ጋር ተቀራርቦ የመስራት ፍላጎት እንዳለውም ነው የገለጹት፡፡
የሞጆ ዋየርና ኬብል ማምረቻ ፋብሪካና የአቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችም ለሃገር ትልቅ አለኝታ የሆኑ ተቋማት መሆናቸውን መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ የባንኩንና የግሩፑን ትስስሮሽ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ መሰረት ደስታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የግሩፑ ዋነኛ ኣጋር ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝ አረጋግጠው በቀጣይም በትብብር መስራቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ከባንኩ ጋር እየተሰሩ የሚገኙ በሂደት ላይ ያሉ ተግባራትም እንዲፋጠኑ ጠይቀዋል፡፡
የሁለቱ ተቋማት ማኔጅመንት በቀጣይ ለባንኩ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ትስስሮሹና የሚለዩት የድጋፍና ትብብር መስኮች ላይ ምክክር የሚካሄድበት መድረክ እንደሚመቻች ከመግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡