ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እና ኒው ሆላንድ ካምፓኒ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

መጋቢት 26፣2016 ዓ.ም-አ.አ
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና  የኒው ሆላንድ ካምፓኒ  የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ ቢዝነስ ዳይሬክተር ኦዝካን ኢረን ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት 500 ትራክተሮችንና 50 ኮምባይነሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አምርቶ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ስሌይማን ደደፎ በመልዕክታቸው የሃገራችን ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ የተመሰረተ ነው፤በመሆኑም ግብርናችንን ለማዘመን ዘመናዊ መሳሪያ ማቅረብ ይኖርብናል ብለዋል፤ አክለውም ተቋማችን ይሄን ለማሳካት ከኒው ሆላንድ ካምፓኒ ጋር በጋራ ለመስራት ወስኗል፡፡ በቀጣይም ማሽኖቹ በሀገር ወስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ ራዕይ ይዘናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተለይም በግብርናው ዘርፍ፣  የገበያ ፍላጎት ለማሟላት የሁለቱ ተቋማት ጥምረት አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ትራክተርና ኮምባይነሮቹ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስር በሚገኘው አዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ እንደሚገጣጠሙ የተገለፀ ሲሆን ሰላሳ ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግባቸዋል ፡፡
የኒው ሆላንድ ካምፓኒ  ቢዝነስ ዳይሬክተር ኦዝካን ኢረን በኢትዮጵያ በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ከተሰማራው ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር በጋራ በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ይህ ገና ጅማሮ ነው ያሉት ሀላፊው ከሁለቱ ተቋማት የጋራ ተጠቃሚነት ባለፈ ይበልጥ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ለገበሬው ማህበረሰብ እጅግ እንደሚጠቅም ገልጸዋል፡፡
የኒው ሆላንድ ካምፓኒ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ ካምፓኒ ሲሆን ከ125 ዓመታት በላይ ገበሬዎችን በግብርና ቴክኖሎጂ ሲደግፍ የቆየ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *