የኮሚቴው አባላት በግሩፑ ስር የሚገኙትን ኢንዱስትሪዎች ለሁለት ቀናት ተዘዋውረው ከጎበኙ በኋላ የማጠቃለያ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት አባላቱ እንደገለጹት ግሩፑ ከሶስት አመታት በፊት ኪሳራ ውስጥ እንደነበር አስታውሰው አሁን ትርፍ ማስመዝገብ መጀመሩ የሚበረታታ ነው፡፡
ከሃገራዊ ለውጡ በፊት ያለ በቂ ጥናት ተገዝተው እየባከኑ የነበሩ የተለያዩ ግብአቶችን ወደ ሃብት የመቀየሩ ስራም ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸው ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥል ብለዋል፡፡
ከደንበኞችና ከባለድርሻ ኣካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር፣የፋብሪካዎች ትስስር፣የምርት ሰርተፊኬሽን፣ የማስተዋወቅ ስራዎችና የምርምር ስራዎች በትኩረት ሊሰራባቸው ይገባል የተባሉ ናቸው፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕ/ር መሃመድ አብዱ ለግሩፑ ሁለንተናዊ ስኬት ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን ድጋፍ እንደሚደርግ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በበኩላቸው እንደገለጹት ግሩፑ ከነበረበት ቀውስ ወጥቶ ትርፋማና ለሃገር የሚጠቅም ተቋም ለማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
የውጭ ምንዛሬ እጦት ግሩፑ ባለው አቅም ልክ እንዳያመርት እንቅፋት እንደሆነበት አስታውሰዋል፡፡
በቀጣይ ኢትዮጵያዊ የሆነ ምርት በማምረት እና ግሩፑን ትክክለኛ የአምራች ቁመና እንዲኖረው የተለያዩ ስራዎች እየተተገበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
መንግስት ድጋፉን የበለጠ አጠናክሮ ውጤታማ የሚኮንበትን እገዛ ሊያደረግ እንደሚገባው ጠቅሰዋል፡፡
የታጠቅ ትራንስፎርመር ማምረቻ ፋብሪካ፣አዲስ ማሽንና መለዋወጫ ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፣የሞጆ ዋየርና ኬብል ፋብሪካና የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትዎች ጉብኝት ተካሄዶባቸዋል፡










