በውይይቱ የግሩፑ የወስጥ ኦዲት አገልግሎት አፈጻጸም እና አጠቃላይ የሪፎርም፣ የምርት፣ የገቢ ፣ የሽያጭ እና የፋይናንስ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ግሩፑ በሪፎርም ስራ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የቆየ ያልተወራረደ የውጭ ምንዛሬ ሂሳብ (LC) በማወራረድ፤ የውጭ ኦዲትን ለማጠናቀቅ በተሰራው ስራ እንዲሁም የቆዩ የህግ ጉዳዮችን በድርድር በመፍታት ያስመዘገበው ውጤት አበረታች ውጤት የተገኘበት እንደሆነ ተገምግሟል፡፡
የነዚህ ስራዎች ወደ መጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸው ለግሩፑ ከፍተኛ አቅም እና ተወዳዳሪነትን የሚያስገኙለት መሆኑ በውይይቱ የተነሳ ሲሆን ቀሪ ስራዎች ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተገምግሟል፡፡
በ6 ወር የታቀደ የምርት ዕቅድ በአማካይ 87.86% ማሳካት ተችሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት የግሩፑ ኢንዱስትሪዎች በነበረባቸው የምርት ግብዓት እጥረት
የምርት አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ እንደነበር የተገመገመ ሲሆን የግብዓት እጥረቱን ተጽዕኖ ለመቋቋምም የኢንዱስትሪዎች የውስጥ ለውስጥ ምርት ትሥሥር ማጠናከር፤ ከሀገር ውስጥ መሟላት የሚችሉ ግብዓቶችን ከሃገር ውስጥ በማሟላት የምርት ሂደቱ እንዲሻሻል በማድረግ የምርት አፈጻጸሙ እየተሻሻለ እንዲመጣ ተደርጓል፡፡ የግማሽ ዓመቱ የምርት አፈጻጸም የ16 በመቶ መጨመር አሳይቷል፡፡
ባጠቃላይ የምርት፣ የሽያጭ እና የትርፍ አፈጻጸሙ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እድገት መመዝገቡ አበረታች እንደሆነ ታይቷል፡፡
በውስጥ ኦዲት የተገኙ ግኝቶች እየቀነሱ መምጣታቸው የተገመገመ ሲሆን በቀጣይ ወደ ዜሮ ለማውረድ መሰራት አለበት ተብሏል፡፡
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኮ/ል ሸጋው ሙሉጌታ በማጠቃለያቸው እንዳነሱት ግሩፑ በዋና ዋና የሪፎርም ስራዎች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ግሩፑ ከነበረበት የኋላ ቀውስ እየወጣ እየሄደ እንደሆነ፤ ለሃገርና ለመንግስት ተስፋ የሚሆን ተቋም እንደሆነ የመጡት ለውጦች አመላካች መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ተቋሙን ሞዴል ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ በመግለጽ በ3ኛ ሩብ አመት በሁሉም መስኮች ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡










