ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከቻይናው ትሩማክስ ኩባንያ ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱ ሚያዝያ 10 ቀን 2014 አ.ም በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በዱባይ ተፈርሟል፡፡
የቦርድ አባላት፣የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፣የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ በፊርማ ስነ ስርአቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ በዋነኛነት በኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን የረጅም ጊዜ የቴክኖሎጂ አጋርነትና በጋራ መስራት ላይ ያለመ ነው፡፡
የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ላይ እሴት በመጨመርና ከሃገር ውስጥ አምራቾች ጋር በመተሳሰር ዘርፉን ለማሳደግም እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ ኩባንያዎች በጋራ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን የመገጣጠምና የማምረት ስራን ለማከናወን ይችላሉ፡፡
የሁለቱ ኩባንያዎች አብሮ መስራት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ፍላጎት ለማሳካት እና በዘርፉ የስራ እድልን ለመፍጠር ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለዘርፉ እድገት ያስቀመጠውን ማበረታቻ በመጠቀም ኩባንያዎቹ የሃገር ውስጥ ገበያን በመሸፈን የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ይሰራሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር ለአፍሪካ ገበያም በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ትሩማክስ ብራንድ የሆኑ የኮንትራክሽን ማሽነሪዎችን ለአለም በማቅረብ የሚታወቅ ኩባንያ ሲሆን በተለይ በጥራትና በድህረ ሽያጭ አገልግሎት ላይ ቀዳሚነትን የያዘ ኩባንያ ነው፡፡