ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እና ኦሮሚያ ባንክ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሱሌይማን ደደፎ (አምባሳደር) እና የኦሮሚያ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተፈሪ መኮንን ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት ሁለቱም ተቋማት ለአንድ አላማ ለሀገር እድገት የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያፋጥን እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በመልእክታቸው ሁለቱም ተቋማት የህዝብ ሀብት መሆናቸውን አንስተው በሀገሪቱ እድገትና ልማት ውስጥ በጋራ መስራታቸው ለስኬታማነት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡አክለውም ግሩፑ ለምርት የሚያስፈልገውን ጥሬ እቃ ከፋተኛ በሆነ የውጭ ምንዛሬ እንደሚገባ ገልጸው ለዚህም ባንኩ በሀገሪቱ የተቀላጠፈ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ በመሆኑ በጋራ ለመስራት ወስነናል ብለዋል፡፡
ከባንኩ ጋር በጋራ መስራታችን የኢትዮጵያን ልማት ለማፋጠን፣ድህነትን ለመቀነስ ብሎም በተቋማችን ያለውን የፋይናንስ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተፈሪ መኮንን ስምምነቱ ለሀገርም ሆነ ለሁለቱ ተቋማት ተልዕኮ መሳካት ሚናው የላቀ መሆኑን ጠቅሰው ባንኩ ለገቢ ግዥዎች የሚፈፅማቸው ክፍያዎች ፈጣን መሆናቸው ትብብሩን ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለዋል።
ስምምነቱ በኦሮሚያ ባንክ ዋና መስሪያቤት የሁለቱም ተቋማት አመራሮች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

