ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ወደ ዘመናዊ አሰራር ለመግባት የሚያስችለውን የኢ.አር.ፒ ሲስተም ለመዘረጋት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

የውል ስምምነቱን የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶቃ ፈርመዋል፡፡
የሚዘረጋው ቴክኖሎጂ አጠቃላይ የሰው ሃብት አስተዳደር ስራዎችን በማዘመን ውጤታማነትን የሚያመጣ ነው፡፡


የንብረት አስተዳደር ስራዎችን የሚያቀላጥፍ፣የፋይናንስ ስርአቱን በመቆጣጠርም ቀልጣፋ እና ግጽነት ያለው ስርአትን የሚዘረጋ መሆኑን የአስተዳደሩ ም/ል ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርአያስላሴ በፊርማ ስምምነቱ ወቅት አብራርተዋል፡፡
ሲስተሙ የመዝገብ ቤት ስራዎችን አውቶሜት በማድረግ ዶክመንቶች በአግባቡ እንዲጠበቁም ያስችላል ብለዋል፡፡


የሽያጭ መረጃዎችን ማስተዳደር፣የተሸከርካሪ አስተዳደር፣የምርት አስተዳደር እና የጥራት ቁጥጥር ስራዎች በሲስተሙ የሚዘምኑ ናቸው፡፡
የአቅድ አፈጻጸምና የምዘና ስርአት እንዲሁም የፕሮጀክት አስተዳደር ስራዎች የተካተቱበት ነው፡፡


በፊርማ ስምምነቱ ወቅት የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን እንዳሉት የአሰራር ስርአታችንን ለማዘመን እና የጀመርነውን ሪፎርም ለማሳለጥ የሲስተሙ መዘርጋት አይነተኛ ሚና አለው፡፡


ሲስተሙን ሃገር በቀል በሆነው ተቋም በማሰራታችን ደግሞ የበለጠ ደህንነቱ የተረጋገጠ ቴክኖሎጂ እንዲኖረን ያስችላል ነው ያሉት፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶቃ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እያካሄዳቸው የሚገኙትን የሪፎርም ስራዎች በማድነቅ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ የሚሆን ቴክኖሎጂ እንዘረጋለን ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *