የውይይቱ አላማ መሃንዲሶቹ ግሩፑ ይዞ የተነሳውን ተልእኮ ከማሳካት አንጻር ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማነሳሳት ያለመ ነው፡፡
በግሩፑ በተለያዩ የምህንድስና ዘርፎች የሰለጠኑ ከ450 በላይ ባለሙያዎች እንደሚገኙ በቀረበው የውይይት መነሻ ጽሁፍ ላይ ተዳሷል፡፡
እነዚህ ባለሙያዎች እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ለማዳበር ያለፉበት መንገድ፣ ያከናወኗቸው ተግባራት፣ የገጠሟቸው ተግዳሮቶችና ወደፊት የሚጠበቁ ውጤቶች በመነሻ ሃሳቡ ላይ የቀረቡ ናቸው፡፡
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ መሃንዲሶቹ ግሩፑና ሃገሪቱ ይዛ ለተነሳቸው ግቦች ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፡፡
በተለይ የፈጠራ ስራ ላይ ትኩረት በማድረግ ሃገር በቀል የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲመረቱ ሚናቸውን ሊጫወቱ ይገባል ብለዋል፡፡
ግሩፑ “ኢትዮጵያ የራሷ ብራንድ ይገባታል” የሚል መሪ ሃሳብ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው ሃሳቡ እውን እንዲሆን የግሩፑ መሃንዲሶች ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሃገር የገጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለግሩፑ ፈተና ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ፈተናዎችን ወደ መልካሚ አጋጣሚ በመቀየር ከውጭ ምንዛሪ ጥገኝነት ለመላቀቅ ጥረት መደረግ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡
ባለሙያዎቹም የተጣለባቸውን ተልእኮ ለመወጣት ዝግጁነታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ተግዳሮት የሆኑባቸውን ጉዳዮች እና የመፍትሄ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡
በቀጣይ በውይይቱ ላይ የተነሱትን ሃሳቦች ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን በመፍጠር በጋራ ለመስራት ከመግባባት ላይ ተደርሷል፡፡






