በኢትዮ ኢንጂነሪነግ ግሩፕ የአዳማ የግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የገጣጠማቸውን ትራክተሮች ለሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስረክቧል፡፡
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ እና አዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የ20 ትራክተሮች ምርት አቅርቦት በቅርቡ መፈራረማቸውን ተከትሎ በዛሬው እለት አስር ዘመናዊ የእርሻ ትራክሮች ከማረሻ እና ከመከስከሻ ጋር የማስረከብ ስራ ተከናውኗል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮ ኢንጂሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢ/ር ሸጋው ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ ግሩፑ ለሲዳማ ክልል ትራክተሮችን ከማስረከብ በተጨማሪ የተሟላ የድህረ ሽያጭ አገልግሎት በቅርበት ለመስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በአሁኑ ወቅት የውሃ ፓምፖችንና አነስተኛ የፈረስ ጉልበት ያላቸውን ትራክተሮች ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ በመጀመሪያ ዙር ለመተካት የማምረት ስራ መጀመሩንና በቀጣይም ምርቶቹን በራሱ ብራንድ በስፋት ለማምረት በሰፊው እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሽመልስ ጥላሁን(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢንዱስትሪው ትራክተሮችን፣ ማረሻዎችንና መከስከሻዎችን የማምረትና የመገጣጠም ሥራ በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በቀጣይ ከክልሉ ጋር በግብርና ማሽነሪዎች አቅርበት ላይ በቅርበት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ ግብርና የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን አስታውሰዋል። የግብርና ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግ ከኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ጋር የሚደረገው ቅንጅታዊ አሰራር ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡







