ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በካሊድ ፋውንዴሽን በትናንትናው ምሽት የኢፍጣር ፕሮግራም አካሄደ፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ ፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ፣ የስራ ሃላፊዎችና በዋናው መስሪያ ቤት የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ተሳትፈዋል፡፡
ግሩፑ በፋውንዴሽኑ ባካሄደው የኢፍጣር እራት ፕሮግራም 150 ደጋፊ የሚሹ የእምነቱ ተከታዮች ተሳትፈዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ ባስተላለፉት መልእክት መሰል የመደጋገፍ ባህሎች ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
አክለውም ፋውንዴሽኑ እየሰራ ያለውን በጎ ተግባር ሁሉም ኣካላት ሊደግፉት ይገባል ብለዋል፡፡
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው በእለቱ የተደረገው ድጋፍ በግሩፑ ማህበራዊ ሃላፊነት ፕሮግራም መሰረት የተከናወነ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በተለያዩ አከባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ መቻሉን በማስታወስ መሰል በጎ ተግባራት በግሩፑ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
የፋውንዴሽኑ መስራች ወንድም ካሊድ በበኩሉ ለተደረገው ድጋፍ በማመስገን እንዲህ አይነት እሴቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉም ህብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፏል፡፡