ኢትዮ ቴሌኮምና ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ምክክርና ጉብኝት ተካሄደ፡፡
ሁለቱ ተቋማት የምርትና የአገልግሎት ትስስር ለመፍጠር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የጀመሩ ሲሆን በዛሬው እለትም በግሩፑ ስር የሚገኘውን የኤሌክትሮኒክስ ኢኩፕመንት ማምረቻ ኢንዱስትሪን ጎብኝተዋል፡፡
ኢንዱስትሪው የተለያዩ የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችለውን አቅም አስጎብኝቷል፡፡
ከዚህ ቀደም ቴሌብዥን፣ስማርት ኢነርጂ ሜትር፣ ፒኪዩ ማስተር፣ ሴኩሪቲ ካሜራ እና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ማምረቱ የተብራራ ሲሆን ፤
ታብሌትና ካሽ ሪጂስተር ማሽን በማምረት ወደ ገበያ ለመግባት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ተብራርቷል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ልኡካን ቡድን አባላት በተለይም ስማርት ስልኮችን በጋራ መስራት እንደሚቻል አንስተዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ካሉት 70 ሚሊየን ደንበኞች ውስጥ 40 በመቶው ብቻ የስማርት ስልክ ተጠቃሚ ሲሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ ስማርት ስልኮችን ለደንበኞቻቸው ማቅረብ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሴኩሪቲ ካሜራ እና የስማርት ሜትሮች ላይ በጋራ መስራት የሚቻልባቸው የትብብር መስኮች ተብለው እስካሁን የተለዩ ናቸው፡፡
የትራንስፎርመር እና የማንሆል ምርት እንዲሁም የሼዶች ግንባታም ከትብብር ማእቀፍ ውስጥ የተያዙ ናቸው፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ የመግባቢያ ስምምነት በመፈረም እና የትብብር ማእቀፉን ሙሉ በሙሉ በመለየት በጋራ ለመስራት የተቋማቱ ሃላፊዎች ከመግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡