ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እና ኤሌክትሪፋይ ኢትዮጵያ ኃ.የተ.የግ.ማ በስትራቴጂካዊ አጋርነት ለቴክኒክ ድጋፍ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አቅርቦት ሥርዓት፣ የባትሪ ሃይል ማከማቻ ስርዓት እና አስፈላጊ አካላት ለማምረት በኢትዮጵያ ውስጥ የማምረቻ ተቋማትን ለማቋቋም የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የኤሌክትሪፋይ ኢትዮጵያ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተስፋዬ አበበ ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ መሰረት ኤሌክትሪፋይ ኢትዮጵያ ኩባንያ የኢቪ መለዋወጫዎችን ከውጭ ምንጭ ወደ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ለማምረት የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ሽግግርን የሚያመቻች ሲሆን የማኑፋክቸሪንግ ተቋማትን ለማቋቋም፣ ለማስፋት እና ቀጣይነት ያለው መሻሻል ለማድረግ የገንዘብ ድጋፍ እና ኢንቨስትመንት ያደርጋል።
ሁለቱም ኩባንያዎች ዘላቂ እና ተወዳዳሪ የማኑፋክቸሪንግ ስነ-ምህዳር በመፍጠር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅዖ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ኤሌክትሪፋይ በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና እና በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማራ የግል ኩባንያ ነው።