ኢኢግ (11/04/17) ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እና የቱርኩ ጁክሮቫ ኩባንያ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች የቴክኖሎጂ አቅርቦት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
የተፈረመው የኮንትራት ስምምነት ክራውለር ኤክስካቫተር፣ ዊል ሎደር እና ባክሆ ሎደር ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ሙሉ ቴክኖሎጂ ለማቅረብ ነው፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የጁኩሮቫ ኩባንያ ጀነራል ማኔጀር ሙስተፋ ያፒሲ ናቸው፡፡
ስምምነቱ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ “ኢትዮጵያ የራሷ ብራንድ ይገባታል” ብሎ ከተነሳው መርህ እና እንደ ሀገርም “ኢትዮጵያ ታምርት” ከሚለው ግብ ጋር በተጣጣመ መልኩ የሚተገበር ሲሆን ግሩፑን የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎቹ ቴክኖሎጂ (ላይሰንሲንግ) ባለቤት የሚያደርገው ነው፡፡
በኮንትራት ስምምነቱ ውስጥ የቴክኖሎጂውን ትግበራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጀመር እንዲቻል 30 ማሽኖች እና መለዋወጫዎች በሲኬዲ እና በኤስ ኬዲ የሚገቡ ሲሆን ይህም የቴክኖሎጂውን ሽግግር ለማሳለጥ የሚያስችል ነው፡፡ በሂደትም በሎካላይዜሽን እና ጆይንት ኢንጂነሪንግ ምርቱን እዚሁ ለማምረት በስምምነቱ ውስጥ የተካተተ ሲሆን የማሽኖቹን አመራረት ሂደት በተመለከተ ቴክኖሎጂን ለማስተላለፍ የሚያስችሉ የዲዛይን፣ የሰፕላይ ቼይን፣ የምርምር እና ልማት፣ የግብይትና ሽያጭ፣ የጥራት ቁጥጥርና ማረጋገጫ ተከታታይ ስልጠናዎችና የአቅም ግንባታ ቴክኒካዊ ድጋፎች በሀገር ውስጥና ኩባንያው በሚገኝበት ሀገር በንድፈ ሐሳብ እና በተግባር እንደሚሰጡ ተካተዋል፡፡
በግሩፑ ስር በሚገኘው የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የሚተገበረው ስምምነቱ ደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘውን ፋብሪካውን ለማዘመን ፋይዳው እጅግ የጎላ ሲሆን በግሩፑ ስር የሚገኙ ሌሎች ኢንዱስትሪዎችም የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንደሚሆኑበትም ተረጋግጧል።
ፋብሪካው ዘመናዊ የማምረቻ ፋሲሊቲ እንዲኖረው የጁክሮቫ ኩባንያ ሙሉ የማማከርና የድጋፍ ስራ እንደሚሰራም በስምምነቱ ውስጥ የተካተተ ነው፡፡
በኮንትራት ስምምነቱ ወቅት የተገኙት የኢኢግ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አብርሃም በላይ እንደተናገሩት ግሩፑ የተቋቋመበት መሠረታዊ ዓላማን ለማሳካት እንደ ጁኩሮቫ ካሉ ኩባንያዎች ጋር አብሮ መሥራት ስለሆነ በዛሬው ዕለት ግሩፑ የተፈራረመው ስምምነት አላማውን ዕውን የሚያደርግ በመሆኑ ለትግበራ ስኬቱ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በስምምነቱ ወቅት የቱርክ ኤምባሲ ተወካዮች፣የግሩፑ የቦርድ አመራር አባላትና የግሩፑ ም/ል ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ተገኝተዋል፡፡





