አስተዳደሩ የግሩፑን የ3 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲገመግም የገንዘብ ሚኒስቴር አባላትና የግሩፑ ስራ አመራር ቦርድ አባላት ተገኝተዋል፡፡
ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባደረገው የሪፎርም ስራ የ2017 1ኛ ሩብ አመትን ጨምሮ ባለፉት ሁለት አመታት ትርፍ ማስመዝገቡ ቀርቧል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረት የፈጠረው የግብአት ችግር ለግሩፑ ፈተና ቢሆንም የውስጥ አቅምን አሟጦ በመጠቀም ግሩፑን ትርፋማ ማድረግ መቻሉም ተብራርቷል፡፡
ከግል ባንኮች ጋር በመቀራረብ የተሰራው ስራም ግሩፑ የተወሰኑ ግብአቶችን እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እንዳብራሩትም መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ በማስቀጠል ግሩፑ የተጣለበትን ተልእኮ እንዲወጣ ማድረግ ይገባዋል፡፡
ከግሩፑ ጋር እየሰሩ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ በማጠናከር የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደርም አፈጻጸሙን መሰረት ያደረገ ግብረ መልስ አቅርቧል፡፡
በዚህም ግሩፑ ምቹ የስራ አከባቢን ከመፍጠር አኳያ ዋና መ/ቤቱን አድሶ ስራ መጀመሩ፤የሰው ሃይል አደረጃጀቱ ጾታን ያማከለ መሆኑ በጥንካሬነት የታዩ ናቸው፡፡
ትርፋማነቱን ለማሰቀጠል ምርቶች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበትና አስተማማኝ እና ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ ሊኖረው እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ም/ል ዋና ዳይሬክተርና የስርአት ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ዝናቡ ይርጋ በማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት የህዝብ ተቋም የሆነውን ግሩፑን ተወዳዳሪና ትርፋማ ለማድረግ ርብርብ ማድረግ ይገባል፡፡
አሁን ላይ ተስፋ ሰጪ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝም በመግለጽ ውስጣዊና ውጫዊ ተጽእኖዎችን በመቋቋም በቀጣይ የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ ይገባል ብለዋል፡፡









