ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን ወደ እምርታዊ ለውጥ ለማሸጋገር እየተካሄደ ያለው ስራ ሊፋጠን ይገባል ተባለ፡፡
ይህ የተባለው የግሩፑ የ2014 አ.ም የመጀመሪያ ግማሽ አመት አፈጻጸም ላይ የውሳኔ ሰጪ ማኔጅመንት አባላቱ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡
በዚህ ወቅት ግሩፑ ባለፉት የለውጥ አመታት ያሳካቸው ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው ይህንን ወደ እመርታዊ ለውጥ ማሸጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተመክሯል፡፡
በውስጥ አቅምና በውጪ አማካሪዎች እየተሰራ የሚገኘው የቢዝነስ ፖርቲፎሊዎን ከዳር ማድረስ አንዱ የተመከረበት ጉዳይ ነው፡፡
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ግሩፑን ማሻገር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ለውጤታማነት እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን በፍጥነት መለየት፣ በቶፕ ሌቭል ማኔጅመነት የሚፈቱ ጉዳዮችን በማቅረብና በአጭር ጊዜ የሚፈቱ ማነቆዎች ላይ በማተኮር ግሩፑን ትርፋማ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ከዋነኛ የቢዝነስ ባለድርሻ አካላት ጋር መንግስት የምክክር መድረክ እያዘጋጀ እንደሆነ ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው መድረኩን በአግባቡ በመጠቀም የገበያ ትስስርን እናጠናክራለን ብለዋል፡፡
የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ል ዋና ስራ አስፈጻሚ እንዳወቅ አብቴም ፖርቲፎሊዮውን ከሚያጠናው ኩባንያው ጋር በቅርበት በመስራት ግሩፑን ወደ እመርታዊ ለውጥ ማሸጋገር ይገባል ብለዋል፡፡
የሃብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ገብረ ማርያም በበኩላቸው የለውጡን ምንነት በአግባቡ በመገንዘብና በተገቢው መንገድ ድጋፍ ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው ብለዋል፡፡