ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በትብብር ማእቀፍ በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ምክክር አደረጉ፡፡
በትናንትናው እለት የተቋማቱ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች እና የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ምክክር ተካሂዷል፡፡
ግሩፑ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተለያዩ የሃይል ዘርፍ ምርቶችን ያቀርባል፡፡
በግሩፑ ስር የሚገኙት የፓወር ኢኩፕመንትስ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፣ የኤሌክትሮኒክስ ኢኩፕመንት ማምረቻ ኢንዱስትሪና የአቃቂ ቤዚክ ሜታልስ በዋነኛነት ምርታቸውን ለዚሁ ተቋም ያቀርባሉ፡፡
ትራንስፎርመር፣ፓወር ፋክተር ኮሬክተር፣ኬብሎችና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስና የብረታ ብረት ምርቶች ናቸው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እየቀረቡ ያሉት፡፡
በምክክሩ ላይ የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ይህንን የቢዝነስ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ ሃገር ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ግንኙነቱን ወደ ፓርትነር ሺፕ በማሳደግ ሁለቱንም ተቋማትና ሃገርንም ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ሰፊ የማምረት አቅም ያለው ዋነኛ አጋራችን ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ይህንን አቅም መጠቀም እንዲቻል በአጋርነት መስራት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡
ግሩፑ ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀምና የሃገሪቱ የኤልክትሪክ አገልግሎትን ለማሳደግ እንዲቻል ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጣ ቲም እንዲቋቋም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ቲሙ በአስር ወራት ጊዜ ውስጥ የተጠናከረ ግንኙነት እንዲመሰረትና ትስስሮሹ እንዲጠናከር ሃላፊነት የተሰጠው ሲሆን በዋና ስራ አስፈጻሚዎች ደረጃ ድጋፍና ክትትል እንዲደረግበትም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡