በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የሁለቱ ተቋማት ዋና ስራ አስፈጻሚዎችና የማኔጅመንት አባላት ተካፍለዋል፡፡
በቅርቡ እንደሚፈረም የሚጠበቀው የፓርትነር ሺፕ ስምምነት ሁለቱ ተቋማት በጋራ መስራት የሚችሉበትን ምቹ መደላደል እንደሚፈጥር ተብራርቷል፡፡
በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስር የሚገኙት የአቃቂ ቤዚክ ሜታልስ፣የአዲስ ማሽንና መለዋወጫ ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣የብረታ ብረት ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ ፣የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፣የኢትዮጵያ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ እና የአዳማ የግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በዋነኛነት በፓርትነር ሺፑ የሚታቀፉ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ፓርትነር ሺፑ ሁለቱም ተቋማት እንደ ሃገር የሚጠበቅባቸውን ተልእኮ ለማሳካት ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ግሩፑ የሪፎርም ሂደት ላይ መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደር ምስጋኑ የቢዝነስ ሞዴሉን፣የፕራይሲንግ እና የፕሮሞሽን ሞዴሎችን ጨምሮ የተለያዩ ሪፎርሞች እየተካሄዱ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ለጥምረቱ መሳካት ከልብ እንሰራለን ያሉ ሲሆን ያሉትን እምቅ ሃብቶች በጋራ መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡
ስኳር ኮርፖሬሽን በነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ የተለያዩ ምርቶችን በግብአትነት በመጠቀም ምርታማነቱን ለማሳደግ እንደሚያስችለው ነው በምክክሩ ላይ የተገለጸው፡፡
ኮርፖሬሽኑ በቂ የሆነ የስኳር ምርት ለህብረተሰቡ በአስተማማኝ ደረጃ ለማቅረብ እንዲያስችለው ለፋብሪካዎቹ መለዋወጫና እና ማሽነሪዎችን ከግሩፑ እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡
ግሩፑም ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅሞ ምርታማነቱን ለማሳደግ ያስችለዋል፡፡
በተለይ እንደ ሃገር የገጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግርን ለመሻገር በጋራ መስራቱ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የታቀደውን የአጋርነት ስምምነት የሚያሳልጡ እና ከሁለቱም ተቋማት የተወከሉ የእርሻ ማሽነሪ ቲም፣የብረታ ብረት ማሽነሪ ቲም፣የኮንስትራክሽን ማሽነቲ ቲም እና የፋይናንስ ቲም ለማቋቋም ከስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን ፓርትነር ሺፑም በቅርቡ እንደሚፈረም ይጠበቃል፡፡