በዓመት 10ሺ ትራክተሮችን ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡


በመርሃ ግብሩ ላይ በቀጣይ የፋብሪካ ግንባታውን ለመጀመር የሚያስችል ፊርማ ተፈርሟል፡፡
ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን በመወከል ዋና ስራ አስፈጻሚው አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የYTO-CAMACO ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ሚስተር ሊዩ ፒ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡
በሞጆ ከተማ ሊገነባ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የትራክተር ፋብሪካ በዓመት 10ሺ ትራክተሮችን የሚያመርት ነው።
ፋብሪካውን የሚገነባው በቻይና ቁጥር አንድ የትራክተር አምራች YTO-CAMACO ሲሆን በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት ግንባታውን አጠናቆ ስራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ በስነ ስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ረጂም ጊዜ ያስቆጠረ በመሆኑ ዘመኑ የደረሰበት የግብርና ማምረቻ ፋብሪካ መገንባት አስፈልጎናል ብለዋል።
በአፍሪካ የመጀመሪያ የYTO ማዕከል የሚሆነው ፋብሪካው ለአፍሪካ ገበያ ጭምር ነው ሲሉም አክለዋል።
በቀን 50 ትራክተሮችንና በዓመት ከ10ሺ በላይ ትራክተሮችን የሚያመርት በመሆኑ ለሀገራችን ግብርና የጀርባ አጥንት መሆኑንም አምባሳደር ምስጋኑ ተናግረዋል።
በየክልሉ የሰርቪስ ማዕከላት ለመገንባትና በቀጣይ መገጣጠሚያ ለማድረግም ታቅዷል፡፡
የYTO ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ሚስተር ሊዩ ፒ በበኩላቸው ኩባንያችን የቻይናን ግብርና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዘመናዊ የቀየረ በመሆኑ የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ጋር ለመስራት እዚህ ተገኝተናል ብለዋል።
ፋብሪካው ለብዙዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ሊዩ ፒ በአጭር ጊዜ ገንብተን እናስረክባለን ሲሉ ቃል ገብተዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አብረሃም በላይ ባደረጉት ንግግር የለውጡ መንግስት የመጀመሪያ ትኩረት ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን በአዲስ አስተሳሰብ እንዲመራ ማድረግ እንደሆነ አስታውሰዋል።ከግዥና ችርቻሮ ወጥቶ በአምራችነት እንዲሠማራ ማድረግ በመሆኑ የዛሬው ፕሮጀክትም የዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የፌደራል ተቋማት አመራሮች፣የግሩፑ የቦርድ አመራሮችና የማኔጅመንት አባላት የሞጆ ከተማ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *