ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከቻይናው ዋይ ቲ ኦ ኩባንያ ጋር በአመት 10 ሺህ ትራክተሮችን ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለመገንባት የሚያችለውን የኮንትራት ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱን የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎና የዋይቲኦ ካማኮ ሲኒየር ፕሮጀክት ማናጀር ሚስተር ዋንግ ሰን ፈርመውታል፡፡
ፋብሪካው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ የሚጠናቀቅ ነው፡፡
በቀን 50 ትራክተሮችንና በዓመት ከ10ሺ በላይ ትራክተሮችን የማምረት አቅም ያለው ሲሆን የሃገራችንን ግብርና ለማዘመን ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው፡፡
በፊርማ ስምምነቱ ወቅት የግሩፑ ስራ አመራር ቦርድ ኣባል ወ/ት ያስሚን ወሃብረቢ ስምምነቱ ከዳር እንዲደርስ ለሰሩት የግሩፑ ማኔጅመንት አባላትና ለዋይቲኦ ካማኮ ሃላፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎም ስምምነቱ ሃገሪቱን ከትክክለኛ አምራቾች ተርታ እንደሚያሰልፋት በመግለጽ ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን እንዲሆን ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
የዋይቲኦ ካማኮ ሲኒየር ፕሮጀክት ማናጀር ሚስተር ዋንግ ሰን በበኩላቸው ከዚህ ስምምነት ላይ በመድረሳቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ለኮንትራቱ ተፈጻሚነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱ ግሩፑን በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ የብቸኛ ወኪል(Exclusive right) ባለቤትነትን የሚያረጋግጥለት ነው፡፡
ይህም ሃገሪቱ በዘርፉ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረትና የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳን ያበረክታል፡፡
የኮንትራት ስምምነቱ ከፋብሪካ ግንባታ በተጨማሪ የድህረ ሽያጭ አገልግሎት ማእከልንም ያካተተ በመሆኑ ዘላቂና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲኖር የሚያስችል ነው፡፡
የፋብሪካው መገንባት በተለይም በግሩፑ ስር የሚገኘውን የአዳማ ግብርና ማሽነሪን ትክክለኛ የአምራች ቁመና እንዲኖረው በማድረግ፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር በማምጣት ለብዙዎች የስራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው፡፡
ስምምነቱ የግሩፑን ባለሙያዎች በተግባርና በንድፈ ሃሳብ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ በማሰልጠን በሶስተኛ ወገን የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡

