ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ YTO ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር ከአፍሪካ ትልቁ የትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ሁለቱ ኩባንያዎች በዛሬው ዕለት ያደረጉት የመግባቢያ ስምምነት ትልቅ የትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ በመገንባት ትራክተሮች፣ ተቀፅላዎች እና ኮምባይነሮችን ለማምረት ያስችላቸዋል፡፡
ስምምነቱን በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በኩል ዋና ስራ አስፈጻሚው አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና በዋይ ቲ ኦ በኩል የኩባንያው የአፍሪካ ዳይሬክተር ሊዩ ሁዋጂን ፈርመዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው አምባሳደር ምስጋኑ ከኩባንያው ጋር የነበረውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ታሪካዊ ስምምነት መሆኑን አንስተው በአጭ ጊዜ ውስጥ ፋብሪካውን እውን ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ሜድ ኢን ኢትዮጵያ የሆኑ ትራክተሮችን እስከ ማምረት የደረሰ ትብብር እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የዋይ ቲ ኦው የአፍሪካ ዳይሬክተር ሊዩ ሁዋጂን በበኩላቸው ግሩፑ በጋራ ለመስራት እድል መስጠቱን በማድነቅ ለትብብሩ ውጤታማነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን በዘርፉ የአፍሪካ ትልቁ የትራክተር መገጣጠሚያ መስመር ባለቤት የሚያደርገው ሲሆን የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻውን ከማሳደግ ባሻገር የአፍሪካ ገበያን መቆጣጠር ያስችለዋል፡፡
የአዲሱ ፋብሪካ ዓመታዊ የትራክተር ምርቱም 10,000 ትራክተሮች ይሆናል፡፡
YTO በዓለም አቀፍ ደረጃ በትራክተር ምርቶች ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ ሲሆን ምርቶቹ በ140 ሀገራት የተሸጡ እና ከ100 በላይ የመገጣጠሚያና ማምረቻ መስመሮች ያሉት ግዙፍ የቻይና ኩባንያ ነው፡፡
አሁን በሃገራችን እየተመረቱ ካሉ ምርቶች በዘለለ በቀጣይ በፀሐይ እና ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ሾፌር አልባ ትራክተሮችን ለማምረት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግር ይኖራቸዋልም ተብሏል፡፡